Fana: At a Speed of Life!

የዳያስፖራ አደረጃጀቶች የእውቅና መርሐ ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጀመሪያው የዳያስፖራ አደረጃጀቶች የእውቅና መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እንድሪስ፣ ዳያስፖራዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በመርሐ ግብሩ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በጎ ተሳትፎ ያደረጉ እና ከ25 ሀገራት የተውጣጡ 52 የዳያስፖራ አደረጃጀቶች እና አባላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

በመርሐ ግብሩ ወቅት ፕሬዚዳንት ሣኅለ ወርቅ ዘውዴ እንደገለጹት÷ እውቅናው ለሀገራቸው በጎ ስራ እየሰሩ ለሚገኙና በመላው ዓለም ለሚገኙ የዳያስፖራ አባላት ሁሉ ነው።

ኢትዮጵያ ለአገራቸው መልካም ነገር የሚያከናውኑ አካላትን እንደምታስታውስ ጠቅሰው÷ መንግስትም ዳያስፖራው ከሀገሩና ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል።

ሀገሪቱ ያለፉትን ዓመታት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ማለፏን አስታውሰው ÷ የዳያስፖራው ማህበረሰብ በሰላም ግንባታና በመልሶ ማቋቋም ስራ ላይ ሀገሩን እና ህዝቡን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ÷ ዳያስፖራዎች ኢትዮጵያ ችግርና ፈተና በገጠማት ጊዜ ለሀገራቸው የሰሩት ስራ በወርቃማ ብዕር የሚፃፍና ሁሌም በታሪክ የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

ዳያስፖራው ከዚህ ቀደም የነበረውን ተሳትፎ ይበልጥ በማሳደግ በሀገሪቱ እየተከናወነ ባለው የሰላም ግንባታ ላይም በጎ ሚናውን በመወጣት የሀገር አለኝታነቱን ዳግም እንዲያረጋግጥ ጥሪ አቅርበዋል።

ዳያስፖራው ለሀገሩ እያሳየ ላለው ተሳትፎ ቀጣይም እውቅና እንደሚሰጥ የገለጹት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እንድሪስ÷ ተመሳሳይ መድረኮችም እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ የሁሉንም ዳያስፖራ ማህበራት ማህደር የያዘ መፅሀፍም በይፋ መመረቁን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.