Fana: At a Speed of Life!

የወር አበባ ጊዜ ህመም አይነቶች፣መንስኤ እና መፍትሄ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የወር አበባ ጊዜ ህመም (Dysmenorrhea) የወር አበባ በሚመጣበት ጊዜ የሚያም ህመም ነው፡፡

ህመሙም ለሁለት እንደሚከፈል ነው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአጠቃላይ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስቱ ዶክተር ሸምሴ ሸውሞሎ የሚናገሩት፡፡

በዚህም የመጀመሪም “ፕራይመሪ ዲስሜኖሪያ “የሚባል ሲሆን÷ እሱም የወር አበባ በመጣ ጊዜ ብቻ የሚሰማ ህመም መሆኑን ገልፀዋል፡

ይህም የሴት ልጅ ሰውነት በየወሩ “ፕሮስታግላንዲን” የሚባል ሆርሞን ስለሚያመነጭ በዚህም ማህፀን እንዲኮማተር ስለሚያደርግ ህመም ይፈጥራል ነው የሚሉት፡፡

በዚህም ከሌላ ህምም ጋር ያልተያያዘና አብዛኛው ሴቶች ላይ የሚታይ እና መደበኛ ህመም መሆኑንም ይናገራሉ፡፡

ሁለተኛው ደግሞ “ሰከንዳሪ ዲስሜኖሪያ”የሚባል የወር አበባ ጊዜ ህመም ሲሆን÷ ከሌሎች ህመሞች ጋር የተያያዘ ለምሳሌ የማህፀን እጢ፣ የማህፀን ውሃ መቋጠር (ovarian cyst)፣ የማህፀን ኢንፌክሽንና ሌሎች ህመሞች ካሉ እና ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚሰማ ህመም መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ይህም ሌሎች ችግሮችን ተከትሎ የመጣ የወር አበባ ጊዜ ህመም መሆኑን ነው ዶክተሩ ያነሱት፡፡

በአብዛኛው ሴቶች ዘንድ የወር አበባ ሊመጣ አንድ ወይም ሁለት ቀን ሲቀር እንዲሁም መፍሰስ ሲጀምር የተወሰነ ህመም ይኖራል የሚሉት ዶክተር ሸምሴ ፤ ህመሙም መደበኛ እና በ72 ሰዓት ውስጥ የሚጠፋ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ውጭ ከሆነ እና ህመሙ ከበድ ያለ ሆኖ ከ72 ሰዓት ከበለጠ፣ ከትምህርት ቤት፣ ከስራ እንዲሁም ከሌሎች የእለት ተእለት እንቅስቃሴ የሚያስቀር ከሆነ ፣ ማስመለስ ፣ ትኩሳት ካለው ወደ ጤና ተቋም መሄድ ይገባል ይላሉ፡፡

መደበኛ የሆነ የወር አበባ ጊዜ ህመም ምልክቶችም ከእንብርት በታች ቁርጠት ፣ የተወሰነ የጀርባ ህመም ፣ ወደ ታፋ አካባቢ የህመም ስሜት ፣አንዳንድ ጊዜም ማቅለሽለሽ ሲሆኑ ህመሙ በጣም የተጋነነ ከሆነና ትኩሳት ካለው ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ገለፃ መደበኛ የወር አበባ ጊዜ ህመምን ለማስታገስ ለብ ያለ ውሃ እቃ ውስጥ አድርጎ ሆድ እና ጀርባ ላይ መያዝ ፣እረፍት ማድረግ እንዲሁም ማስታገሻዎችን መውሰድ ይመከራል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.