Fana: At a Speed of Life!

የአሜሪካ ጦር በሶማሊያ የአይ ኤስ መሪ መግደሉን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ጦር በሶማሊያ ከፍተኛ የአይ ኤስ መሪ የገደለበትን ተልዕኮ ማካሄዱን የአሜሪካ ባለስልጣናት ገልፀዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ትናንት በሰጡት መግለጫ÷ የአይ ኤስ መሪ እና ለአይ ኤስ ዓለም አቀፋዊ የትስስር መረብ ዋና አመቻች ተብሎ የተሰየመው ቢላል አል-ሱዳኒ ተገድሏል ማለታቸውን የአልጀዚራ ዘገባ ያመላክታል።

ተልዕኮው በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ተቀባይነት አግኝቶ በፈረንጆቹ ጥር 25 መካሄዱንም ዘገባው አክሏል።

ሚኒስትሩ አያይዘውም አል-ሱዳኒ የአይ ኤስን እንቅስቃሴ በአፍሪካ ውስጥ የማሳደግ እና አፍጋኒስታንን ጨምሮ የቡድኑን ስራዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በገንዘብ ድጋፍ የማድረግ ሃላፊነት ነበረው ብለዋል፡፡

የአሜሪካ ጦር እንዴት ድርጊቱን እንደፈፀመ እና ምን ያህል የአሜሪካ ወታደሮች እንደተሳተፉ የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።

የአሜሪካ ባለስልጣናት ለሬውተርስ የዜና ወኪል እንደገለፁት በወታደራዊ ተልዕኮው 10 የአል-ሱዳኒ ተባባሪዎች ተገድለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.