Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ እና ኔቶ አውሮፓን ሙሉ በሙሉ ወደ ወታደራዊ ግጭት ሊከቷት ነው – ሩሲያ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቅጥ ያጣው የአሜሪካ የተስፋፊነት እና ዓለምን የመቆጣጠር ፍላጎት አውሮፓን የግጭት ማዕከል እያደረጋት ነው ስትል ሩሲያ ወቀሰች።

በአውሮፓ የደኅንነት እና ትብብር ድርጅት ውስጥ የሩሲያ ምክትል መልዕክተኛ የሆኑት ማክሲም ቡያኬቪች ÷ በአሜሪካ እና አጋሮቿ በሆኑት የሰሜኑ ጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት ሀገራት ድጋፍ በዩክሬን አሁንም የቀጠለው ግጭት ቶሎ መቋጫ ካልተበጀለት ጦሱ ለሌሎች ሀገራትም ይተርፋል ሲሉ ለድርጅቱ ቋሚ ምክር-ቤት ማስጠንቀቂያ አዘል ማሳሰቢያ መስጠታቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

አሜሪካ እና የኔቶ አባል ሀገራት ቀዩን መስመር ሊጥሱ እጅግ ተቃርበዋል ሲሉም ነው ያስጠነቀቁት፡፡

ማክሲም ቡያኬቪች አሜሪካ እና አጋሮቿ የአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን የታንክ ድጋፍ ለመሥጠት ያወጡት ዕቅድ ኪየቭን ለመጥቀም ሳይሆን ሆነ ብለው ሀገሪቷ በሩሲያ ሕዝብ ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንድትወስድ በማነሳሳት ብጥብጡ በቀላሉ እንዳይበርድ ለማድረግ እና እሳቱን ከዳር ሆኖ ለመሞቅ ነው ብለዋል፡፡

ነገር ግን እንዳሰቡት የግጭቱ ወላፈን በሁለቱ ሀገራት ብቻ የሚያቆም ሳይሆን የትኛውም ወገን ተጠቃሚ የማይሆንበትን እሳት የሚጭር እና አውሮፓን ባስ ሲልም ዓለምን የሚያቃጥል ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡

አሜሪካን እና ብሪታኒያን አሁን እየተካሄደ ላለው ብጥብጥ ጠማቂዎች ናቸው ሲሉ ሀገራቱን ወንጅለዋል።

አሜሪካ እና ጀርመን ዘመናዊ ታንኮችን ለዩክሬን እንልካለን ሲሉ ማስታወቃቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

ሌሎች የሰሜኑ ጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት አባል ሀገራትም ተመሳሳይ ፍላጎት እንዳላቸው ነው የተጠቆመው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.