Fana: At a Speed of Life!

በግዢ ዙሪያ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 20 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር የጋራ ምክክር መድረክ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እያካሄደ ነው።

መንግስት በየዓመቱ ከሚመድበው ዓመታዊ በጀት 70 በመቶ የሚሆነው በግዢ የሚውል ሲሆን፥ በጀቱ ለታለመለት ዓላማ ይውል ዘንድ በግልፅነት ህግን መሠረት አድርጎ እንዲከናወን የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል ተብሏል።

በመድረኩ ላይ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተሻለ በልሁ፥ የከፍተኛ የትምህት ተቋማት የሚያስፈልጓቸውን የመሠረታዊ ሸቀጦችና የግንባታ እቃዎች ግዢዎችን በግልፅነትና ለታለመለት ዓላማ ብቻ በማዋል በጥንቃቄ ማከናወን እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ በበኩላቸው በግዢ ሂደት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ አስራሮች እየተተገበሩ መሆኑን ገልፀዋል።

በቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተተገበረ የሚገኘው የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ዘዴ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ መተግበር መጀመሩን የገለፁት አቶ ሃጂ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር አብሮ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በምክክር መድረኩ ከግዢ ጋር በተያያዘ የውል አስተዳደር፣ የቅሬታ አቀራረብና አቤቱታ አፈታት እንዲሁም የሚፈጸሙ ግዢዎች ለሃገር ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ሊኖራቸው በሚችለው አስተዋፅኦ ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው።

በተሾመ ኃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.