Fana: At a Speed of Life!

ከ183 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 20 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን ከጥር 12 እስከ 18 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል ከ183 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን አስታወቀ።

ከተያዙት እቃዎች መካከል 144 ነጥብ 9 ሚሊየን የገቢ እንዲሁም 38 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎች ናቸው ተብሏል።

ከዚህ ውስጥ አልባሳት፣ ማእድን፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች ፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻና በጥቆማ የተያዙ ሲሆን የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ስምንት ግለሰቦች እና አምስት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪውን አቅርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.