አሸባሪውን ሸኔ የመደምሰሱ ሥራ እንደታሰበው እየሄደ ነው – የዘመቻው አመራሮች
አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ጉጂ፣ ቦረና ዞን እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አጎራባች አካባቢዎች ሽብርተኛውን ሸኔን የመደምሰስ ዘመቻ እንደታሰበው እየሄደ መሆኑን ዘመቻውን የሚመሩ አመራሮች ተናገሩ ።
በምስራቅ ጉጂ ዞን ሊበን ወረዳ በሽብር ቡድኑ ቁጥጥር ስር የነበሩ ቀበሌዎችን ከጠላት ይዞታ በማላቀቅ ህዝብን የማደራጀት፣ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ወደ አገልግሎት ማስገባት፣ ከሰላም የራቀውን ማህበረሰብ ወደ ሰላም በመመለስ የሰላም ጥብቃ ስራው ባለቤት ማድረግና ተያያዥ ጉዳዮችን ማዕከል ያደረገ ውይይት እየተከናወነ ነው፡፡
ነፃ በወጡ ቀበሌዎችም ዘመቻውን በሚመሩት የመከላከያ አመራሮች የተመራ ልዑክ የዞኑን ከፍተኛ አመራሮች አካቶ ውይይትም ተካሂዷል።
ዘመቻውን የሚመሩ አንድ የመከላከያ ከፍተኛ አመራር እንዳሉት ፥ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተከስቶ የቆየውን የህልውና አደጋ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም አሸባሪው የሸኔ በህዝቡ ላይ በርካታ ጉዳቶችን እያደረሰ ቆይቷል።
ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና ታጣቂ ቡድኑን ከቀጠናው ለማጥፋት የሚያግዝ የዘመቻ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ም ነው የገለጹት፡፡
የዘመቻ መኮንኑ በውጤቱም በዞኑ የሚገኘውን ሊበን ወረዳ ጨምሮ በርካታ ቀበሌዎችን ከጠላት ነፃ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪ በርካታ የጠላት ንብረቶች መያዛቸውን፣ ከህዝብ መሃል ሆነው ለጠላት የሚሰሩ አካላትን መለየታቸውንና ጠላት መልሶ እንዳይደራጅ በማድረግ አቅሙን የማዳከም ሥራ መሠራቱን ሃላፊው አስረድተዋል።
መላው ህዝብ የዚህ ዘመቻ ግንባር ቀደም መሪ በመሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ችግር የሆነውን ሽብርተኛ ሃይል በማጥፋት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴያችን መመለስ ይገባናልም ነው ያሉት።
የምስራቅ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ኡዶ በበኩላቸው ፥ የሸኔ ታጣቂ ቡድን በዞኑ በቃላት ሊገለፁ የማይችሉ ጉዳት በህዝብ ላይ ማድረሱን አስታውቀዋል።
ይህን ችግር እስከ ወዲያኛው ለመፍታት በቀጠናው ያለው የፀጥታ መዋቅር የህይወት መስዋዕትነትን በመክፈል ህዝባዊነቱን እያረጋገጠ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት፡፡
ዋና አስተዳዳሪው አክለውም ፥ ይህ መስዋዕትነት ተፈላጊውን ውጤት እንዲያመጣ የመላው ህዝብ ተሳትፎ ለነገ የማይባል ተግባር በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን ሊዋጣ ይገባል ማለታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።