Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ በሥድሥት ወራት ከ284 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ባለፉት ሥድሥት ወራት ለ284 ሺህ 998 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩን አስታውቋል፡፡
 
በቢሮው የሥራ ስምሪት ማስፋፊያ ዳይሬክተር ሰብሓዲን ሱልጣን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን በርካታ የሥራ አጥ ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
 
በተለይም ወጣቶች ስራ ከመጠበቅ ይልቅ ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ አስፈላጊውን የክህሎት ስልጠና የመስጠት እና የማብቃት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡
 
ቢሮው ባለፉት 6 ወራት 375 ሺህ 515 ስራ ፈላጊ ዜጎችን በአንድ ማዕከል በመመዝገብ 438 ሺህ 590 አማራጭ የሥራ እድል ጸጋዎችን መለየቱን ጠቁመዋል፡፡
 
በዚህ መሰረት በአዲስ አበባ ለ284 ሺህ 998 ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ነው ዳይሬክተሩ ያብራሩት፡፡
 
ከተፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥ 87 ከመቶ ቋሚ እና 13 ከመቶ ደግሞ ጊዜያዊ መሆኑን ጠቁመው÷ ከተጠቃሚዎች ውስጥ 50 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
 
የስራ እድል የተፈጠረባቸው ዘርፎችም ማምረቻ፣ ግንባታ፣ ንግድ፣ ከተማ ግብርና እንዲሁም አገልግሎት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
 
ከሳዑዲ ዓረቢያ እና ከሌሎች ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች የሚመለሱ ዜጎችን ወደ ስራ ለማስገባትም ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.