Fana: At a Speed of Life!

ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በተባሉ አራት የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች ላይ የምስክር ቃል ተሰማ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሲሚንቶ ግዢ ጋር ተያይዞ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ያለአግባብ ለግል ጥቅም አውለዋል ተብለው በተከሰሱ አራት የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች ላይ የምስክር ቃል ተሰማ።

የምስክሮችን ቃል ያደመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ዐቃቤ ህግ ያቀረባቸውን የምስክሮችን ቃል መርምሮ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የምስክር ቃል የተሰማባቸው ተከሳሾች የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ተቋም የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ደሜ፣ በተቋሙ የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ግዢ ዋና ክፍል ኃላፊ አቶ አሸናፊ ተስፋዬ ፣ በተቋሙ የግዢ ባለሙያ ናቸው የተባሉ ቱጅባ ቀልቤሳ እና 4ኛ ተከሳሽ ሙስጠፋ ሙሳ ናቸው።

ተከሳሾቹ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ተቋም የግዢ ፍላጎት ሳይኖረው ትዕዛዝ ባልተሰጠበት እና ከተቋሙ ዕውቅና ውጪ የግዢ ባለሙያ ሆነው ሲሰሩ፥ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በ2013 እና 2014 ዓ.ም በተለያዩ ቀናቶች ለተቋሙ ነው በሚል ከሁለት ፋብሪካዎች የገዙትን 29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ምርት በተለያዩ ቀናቶች ለግለሰቦች በመሸጥ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ሲል ዐቃቤ ህግ ታህሳስ 3 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ስልጣንን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መከሰስረቱ ይታወሳል።

ተከሳሾቹ ክሱ ከደረሳቸውና በንባብ ከተሰማ በኋላ ወንጀሉን አልፈጸምንም ሲሉ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን 3 ምስክሮችን አሰምቷል፡፡

የምስክሮችን ቃል ያዳመጠው ችሎቱ የምስክር ቃል መርምሮ ብይን ለመስጠት ለየካቲት 22 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.