Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ምስጋኑ በኢትዮጵያ ከቻይና እና ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 22 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኢትዮጵያ ከቻይና አምባሳደር ዣኦ ዡዩአን እና ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አምባሳደር መሀመድ ሳሊም አል ራሺዲ ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ከአምባሳደር ዣኦ ዡዩአን ጋር ባደረጉት ውይይት ÷ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አዲሱ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኃላፊነት በመጡ ማግስት የመጀመሪያውን ጉብኝታቸው በኢትዮጵያ  ማድረጋቸው የጠንካራ ግንኙነቱ ዋና ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ በስፋት እንዲሰማሩም አምባሳደሩን ጠይቀዋል፡፡

ሀገራቱ ከአሁን በፊት የተፈራረሙትን ጥቅል የስትራቴጂካዊ ትብብር አጋርነት ስምምነትን  በመተግበር ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ቻይና  አምባሳደር ዣኦ ዡዩአን በበኩላቸው÷ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያላትን ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

የቻይና ባለሃብቶች በብዛት በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ መናገራቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ አምባሳደር ምስጋኑ በኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አምባሳደር መሀመድ ሳሊም አል ራሺዲ ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

በውይይቱ አምባሳደር ምስጋኑ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ባለፈችበት ወቅት ከጎን የቆመች ሁነኛ የልማት አጋር ነች ብለዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በንግድ አጋርነትም ከፍተኛ ድርሻ አላት ያሉት አምባሰደሩ÷ በቀጣይም ሁሉን አቀፍ ትብብሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

አምባሳደር መሃመድ ሳሊም አል ራሺዲ  በበኩላቸው÷ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች  ለሀገራቱ ግንኙነት ልዩ ትኩረት ሰጥተው በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በቀጣይም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለያዩ መስኮች በማስፋት አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.