Fana: At a Speed of Life!

የኩላሊት እና ሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን መንስኤ እና ሕክምና

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኩላሊት እና የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ከኩላሊት እስከ ሽንት ፊኛ ድረስ ያለውን ክፍል የሚያጠቃ ሕመም ነው፡፡

ኢንፌክሽኑ በአብዛኛው የታወቀ ምልክት ቢያሳይም በአንዳንድ ሰዎች ላይ ግን ጭራሽ ምልክት ላያሳይ ይችላል፡፡

የኩላሊት እና የሽንት ፊኛ ኢንፌክሽን በዋናነት በሴቶች ላይ በተለይም ለአቅመ ሔዋን በደረሱት ላይ የሚከሰት ሲሆን፥ አንዳንድ ጊዜም በወንዶች እንዲሁም በሕጻናት ላይ የመከሰት ዕድል እንዳለው ይነገራል፡፡

ምንም እንኳ በቁጥር ደረጃ በሴቶች ላይ ቢበዛም በወንዶች ላይ ሲከሰት ግን ሕመሙ ከሴቶች ይልቅ እንደሚያይል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሕክምና ክፍል የኩላሊት ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ቢኒያም ግርማ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በተፈጥሮ የሴቶች የሽንት ሥርዓት ከወንዶች በበለጠ ሁኔታ ለኢንፌክሽን የተጋለጠ ነው ይላሉ፡፡

በተጨማሪም በብዛት ውኃ አለመጠጣት፣ ከግብረ ሥጋ ግንኙነት ጋር በተያያዘ የሚኖሩ የንጽህና አጠባበቅ ሁኔታ እንዲሁም በሽንት ቧንቧና ፊኛ ላይ የሚደረጉ ሌሎች ሕክምናዎች ከመንስኤዎች መካከል ይጠቀሳሉ ነው የሚሉት።

በአብዛኛው የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሲከሰት፥ ከእምብርት በታች የመቁረጥ፣ ቶሎ ቶሎ ሽንት የመምጣት ስሜት፣ በሚሸናበት ጊዜ ምቾት ማጣት፣ የማቃጠል ስሜት፣ የሽንት ቀለም መቀየር ደም ሊመስል ይችላል እና የተለየ ጠረን ያለው ፈሳሽ ምልክት ይታያል።

የኩላሊት ኢንፌክሽን ምልክቶች በጎን የአካል ክፍል (ኩላሊቶቹ ላይ) የሕመም ስሜት፣ ትኩሳት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ መሆናቸውን እና በአንዳንድ ሰዎች ላይ ምልክት ላይኖረው እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡

ቀላል እና ከባድ ኢንፌክሽኖችን መሰረት ያደረገ ውጤታማ ሕክምና በሀገር ውስጥ እንደሚሰጥ ዶክተር ቢኒያም ተናግረዋል፡፡

ቀለል ያሉት ኢንፌክሽኖች በአብዛኛው በሚዋጡ መድሃኒቶች ከ3 እስከ 7 ቀናት ባለው ጊዜ እንደሚድኑ እና ከባድ ኢንፌክሽኖች ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ ተኝቶ በመርፌ እስከ መታከም የሚደርሱ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡

ኢንፌክሽኑ በወቅቱ ሕክምና ካልተደረገለት አንዳንድ ጊዜ በመድኃኒት እስከማይድንበት ደረጃ እንደሚደርስ በዚህም እስከ ቀዶ ሕክምና እንዲሁም ኩላሊት ንቅለ ተከላ ሊያደርስ እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡

ኢንፌክሽኑ ከኩላሊት ወጥቶ ወደ ደም ስር ከገባ ደግሞ ሕክምናው ውስብስብ እንደሚሆን እና እስከ ሞት ሊያደርስ እንደሚችል ነው የጠቆሙት፡፡

በመሆኑም ማንኛውም ሰው በየዓመቱ የኩላሊት ምርመራ ቢያደርግ በተለይም እንደ ደም ግፊት፣ ስኳር እና ሌሎች ሕመሞች ያሉባቸው ሰዎች ደግሞ እንደየሁኔታው በየስድስት ወሩ የኩላሊት ጤና ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራል ይላሉ ስፔሻሊስቱ፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.