Fana: At a Speed of Life!

ከ6 ሚሊየን ዶላር በላይ በማሸሽ የተጠረጠሩ 6 የጉምሩክ ሠራተኞች ላይ የክስ መመሥረቻ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ በ26 ግለሰቦች እንዲሸሽ በማድረግ የተጠረጠሩ ሥድስት የጉምሩክ ሠራተኞች ላይ የክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ።

ግለሰቦች ሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ በማሳጣት የተጠረጠሩ ናቸው።

ዐቃቤ ሕግ በሥድስቱ የቦሌ ኤርፖርት ቅርጫፍ የጉምሩክ ኮሚሽን ተጠርጣሪ ሠራተኞች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ሊመሰርት መሆኑን ለፍርድ ቤቱ መግለጹን ተከትሎ ነው የክስ መመስረቻ ጊዜ የተፈቀደው።

ሥድስቱ ተጠርጣሪዎች÷ ምትኩ አበባው ፣ ግርማ ይባፋ፣ እንግዳ አቦ፣ ማቲዎስ ከታ፣ ቤተልሔም ንጉሴ እንዲሁም ሜላት መስፍን ይባላሉ።

ተጠርጣሪዎቹ 26 ግለሰቦች በተለያየ ጊዜ ከውጭ ሀገር ይዘው የገቡት የአሜሪካ ዶላር ነው በማለት ‹‹ዲክሌር›› በማድረግ በየደረጃው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የገንዘብ መጠን ቀንሶ፣ ሰርዞና ደልዞ ሲስተም ላይ በማስቀመጥ እንዲሁም ሠነድ በመሰወር በአጠቃላይ ከ6 ሚሊየን በላይ የአሜሪካ ዶላር በግለሰቦቹ እንዲሸሽ አስደርገዋልም ተብለው በመጠርጠራቸው ምርመራ ሲከናወንባቸው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ የምርመራ ሥራውን ሲያከናውን የቆየው የፌደራል ፖሊስ መርማሪ÷ ምርመራውን ማጠናቀቁን እና የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቢሕግ ማስረከቡን ዛሬ ለችሎት አስታውቋል።

የሙስና ጉዳዮች ዳሪክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ÷ ትርጉም የሚፈልጉ ሠነዶችን ገሚሱን አስተርጉሞ በተጠርጣሪዎች ላይ የሙስና ወንጀል ክስ ለመመስረት እንዲያስችለው የ15 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው÷ ትርጉም የሚፈልጉ ሠነዶችን ለማስተርጎም ተጨማሪ ጊዜ አይወስድም ሲሉ ተከራክረዋል።

የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን እና ቋሚ አድራሻ እንዳላቸው ገልጸው የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ እንዲሸሽ በተደረገው የአሜሪካ ዶላር በሀገሪቱ ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቅሷል። ከ10 ዓመት በላይ በሚያስቀጣ አንቀጽ የሚከሰሱ መሆኑን ገልጾ የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሞ ተከራክሯል።

ክርክሩን የተከታተለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የተጠርጣሪዎቹ የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ዐቃቤ ሕግ ከጠየቀው 15 ቀናት ውስጥ 10 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.