ቴህራን አሜሪካ ከጦርነት ቀስቃሽ ድርጊቷ እንድትቆጠብ አስጠነቀቀች
አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ በቴህራን ላይ የምትወስደው ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ ወደ ግልጽ ጦርነት ሊያመራ እንደሚችል የኢራን ዲፕሎማቶች አስጠነቀቁ።
በቅርቡ በኢራን ወታደራዊ ፋብሪካ ከተፈጸመው የድሮን ጥቃት ጋር በተያያዘ አሜሪካ ሳትኖርበት አይቀርም የሚሉ ጭምጭምታዎች ሲደመጡ ቆይቷል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቴህራን ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት በትናንትናው ዕለት እንዳስታወቀው፥ በየትኛውም ደረጃ ወታደራዊ አማራጭን መጠቀም ወደ ጦርነት መግባት ማለት ነው።
ኢራን መሰሉን አካሄድ “በደካማነት” ትመለከተዋለችም ነው ያለው።
ሆኖም አሜሪካ በተሳሳተ ስሌት ጦርነት ከጀመረች መዘዙ ለአካባቢው እና ለሰፊው ዓለም አሳሳቢ እንደሚሆንና ለዋሺንግተንም ሸክሙ እንደሚከብድ አስጠንቅቋል።
መግለጫው የተሰጠው ቅዳሜ ምሽት በኢራን ማዕከላዊ ከተማ ኢስፋሃን የመከላከያ ሚኒስቴር ንብረት ላይ ከደረሰ ጥቃት በኋላ ነው።
በጥቃቱ ፈንጂ የያዙ ሶስት ትናንሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ተሳትፈዋል ተብሏል።
ዎልስትሪት ጆርናልና ጄሩሳሌም ፖስትን ጨምሮ በርካታ የሚዲያ አውታሮች ጥቃቱን እስራኤል እዛው ኢራን ውስጥ ሆና ፈጽማዋለች በሚል ዘግበዋል።
በአንጻሩ እስራኤል ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ የቀረበባትን ውንጀላ ጨምሮ ምንም ያለቸው ነገር የለም።
በኢስፋሃን የደረሱት ፍንዳታዎች የአሜሪካ አየር ሃይል ተልዕኮ ነው የሚል የመነሻ ግምት በአረብ መገናኛ ብዙሃን ዘንድ መሰራጨቱን የአር ቲ ዘገባ ያመላክታል።
ይሁን እንጂ የፔንታጎን ቃል አቀባይ ፓትሪክ ራይደር ኋላ ላይ እንደተናገሩት በጥቃቱ ምንም አይነት የአሜሪካ ጦር አልተሳተፈም ያሉ ሲሆን፤ ተጨማሪ አስተያየት ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።