Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል ለሚካሄደው ሕዝበ-ውሳኔ ስኬታማነት በቂ ዝግጅት ተደርጓል-ቦርዱ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች የሚካሄደውን ሕዝበ-ውሳኔ በተሳካ መልኩ ለማከናወን በቂ ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ÷በደቡብ ክልል ሥር የሚገኙ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ለሚካሄደው ሕዝበ-ውሳኔ ስኬታማ ክንውን በቦርዱ በኩል በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በምርጫ ሂደት የሚያጋጥሙ ጉድለቶች የሚሻሻሉበት እና አፋጣኝ እርማት የሚወሰድበት የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱንም ገልጸዋል።

በሕዝበ-ውሳኔው በነበረው የመቀጠል ወይም በአዲስ መደራጀት በሚሉት ሁለት የተለያዩ አማራጮች ክርክርና ውይይት እንዲያደርጉና የተሻለ የምርጫ ልምምድ እንዲኖር ተሰርቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ እና ሌሎች የሲቪል ማህበራት በምርጫ ሂደቱ መራጮች እንዲሳተፉ በማስተማር እና አፈጻጸሙን እንዲከታተሉ ፈቃድ መሰጠቱንም ተናግረዋል።

ለምርጫ አስፈጻሚዎች ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች በ31 ማዕከላት እንዲደርሱ የማጓጓዝ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም ሕዝበ-ውሳኔውን ለማካሄድ በቂ ዝግጅት መደረጉንና የድምፅ አሰጣጡን ለማከናወን የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውንም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ደራሼ) ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም የሕዝበ- ውሳኔ የድምፅ አሰጣጥ የሚከናወን መሆኑ ታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.