የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች እንደማያቋርጥ ገለፀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጣቸውን የኦፕሬሽን አገልግሎቶች የማያቋረጥ መሆኑን ገለፀ።
አገልግሎቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ በኮሮናቫይረስ /ኮቪድ-19/ ወረርሽኝ ምክንያት ከወትሮ በተለየ በየአገልግሎት መስጫ ማዕከሎቹ በአገልግሎት ፈላጊ ደንበኞች ቀጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጿል።
በአብዛኛው ክልሎችና በአዲስ አበባ በሚገኙ አንዳንድ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት በተደረገው ምልከታ በተለይ የቅድመ ክፍያ ካርድ ለማስሞላት በርካታ ደንበኞች በየቀኑ ረጅም ሰልፎች ተሰልፈው መመልከቱን አስታውቋል።
አብዛኛው ደንበኞች የቅድመ ክፍያ ቆጣሪያቸው ሂሳብ እያለውም ተቋሙ አገልግሎት ሊያቋርጥ ይችላል በሚል ፍርሃት ቀድመው ለመሙላት እየተሰለፉ እንደሚገኙም ነው ያስታወቀው።
ይህ ደግሞ አሁን ከተከሰተው ወረርሽኝ አኳያ መሰል ሰልፎች ለበሽታው የሚያጋልጥ መሆኑ መገንዘብ እንደሚያስፈልግም አስታውቋል።
በመሆኑም የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንኞቹ የካርድ መሙላትን ጨምሮ ሌሎች የኦፐሬሽን ሥራዎች የማያቋረጥ መሆኑን በመገንዘብ በሚቀርባቸውና ወረፋ በሌላቸው ማዕከላትና እንዲገለገሉ አስገንዝቧል።
የድህረ ክፍያ አገልግሎት ተጠቃ ሚደንበኞቹንም ወርሃዊ የፍጆታ ሂሳባቸውን በዘመናዊ መንገድ በባንክ እንዲከፍሉ ለማድረግ ሰፊሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን በመግለጽ፤ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የሚጀመረም መሆኑንም ገልጿል።