Fana: At a Speed of Life!

የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስን የመጠበቅና የመንከባከብ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ -አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ ዙሪያ ሲከናወኑ የቆዩ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን መርቀው ከፍተዋል ።
 
በምርቃት-ስነ ስርዓቱ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደገለፁት÷ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች መካከል የሀረር ጁገል የዓለም ቅርስ አንዱ ነው።
 
የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ ስጋትና አደጋ አንዣቦበት እንደነበር ጠቁመው ÷ቅርሱን የሚጎዳ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ጉዳት ሲደርስበት እንደነበረ አስታውሰዋል።
 
መሰል ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ የጋራ ግብረ ሃይል በማቋቋምና ለቅርሱ ልዩ ትኩረት በመስጠት የአመለካከትና የህግ ጥሰት ችግሮችን ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።
 
ሆኖም በአጭር ጊዜ ውስጥ በጋራ በመንቀሳቀስ በጁገል አለም አቀፍ ቅርስ ዙሪያ ውጤታማ የአረንጓዴ ልማት ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
 
በሀረር ከተማ የሚገኙ በርካታ ቅርሶችን ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆኑና ከተማውንም ለነዋሪው የተመቸ ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባራት ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
 
ማንኛውም ስራ ያለ ህብረተሰብ ተሳትፎና አጋርነት ውጤታማና ቀጣይነት ሊኖረው እንደማይችል የገለፁት አቶ ኦርዲን ÷ በተለይ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተጀመረውን የቅርስ ጥበቃ፣ የጽዳትና ውበት ስራ እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።
 
የሀረር ከተማ ማዘጋጀት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኡስማኢል ዩሱፍ በጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ ዙርያ 6 ሺህ 114 ካሬ የአረንጓዴ ልማት መከናወኑን ጠቁመው÷ፕሮጀክቶቹም በክልሉ በሚገኙ 16 ሴክተር መስሪያ ቤቶች ያለሙት መሆኑን ገልጸዋል።
 
የጁገል ቅርስ የዓለም፣ የመላው ኢትዮጵያዊ ቅርስ በመሆኑ የከፋ ደረጃና አደጋ ውስጥ ከመግባቱ በፊት በመጠበቅና በመንከባከብ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለብን ማለታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.