የንግድ፣ ልማትና ኢንቨስትመንት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እንዲጠናከሩ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እየተከናወኑ ያሉ የሀገር ገጽታ ግንባታ፣ የንግድ፣ ልማትና ኢንቨስትመንት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የበጀት ዓመቱን ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል።
በሚኒስቴሩ የዕቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ዓለማየሁ ሰውአገኝ÷ የተቋሙን የስድስት ወራት አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል፡፡
ተቋሙ ተልዕኮውን ለመወጣት የአሠራር ማሻሻያ አድርጎ እየሠራ መሆኑን በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረውን ግጭት መነሻ በማድረግ አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት ያልተገባ ጫና ፈጥረው እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡
ጫናውን በመቀልበስና እውነታውን ለዓለም በማሳወቅ ረገድ ሚኒስቴሩ የተሳካ የዲፕሎማሲ ሥራ አከናውኗል ነው የተባለው፡፡
በተጨማሪም በሰላም ስምምነቱ ሂደትና በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ የታየው ቁርጠኝነት ”ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ” ለሚለው እሳቤ መሰረት የጣለ መሆኑንም አምባሳደር ዓለማየሁ ገልጸዋል።
ከዳያስፖራው ጋር በመቀናጀት በሀገር ገጽታ ግንባታ፣ በልማት፣ ኢንቨስትመንትና በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች የተከናወኑ ተግባራት ጉልህ ፋይዳ እንደነበራቸው ጠቅሰዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመሻገር ሚኒስቴሩ የተለያዩ የአሠራር ማሻሻያዎችን ሲተገብር እንደነበር ገልጸዋል።
ከተለያዩ ሀገራት ጋር ኢትዮጵያ ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሟን ባስጠበቀ መልኩ እንዲከናወን ለማድረግ የተሠራው ሥራ ስኬታማ እንደነበርም አስረድተዋል።
በዚህ ረገድ የሀገሪቱን ጥቅም በሚመለከት ያለው ዝግጁነትና ምላሽ የመስጠት ተግባር በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ መከናወኑ አሁን ለደረሰችበት መልካም ሁኔታ የጎላ ሚና ነበረው ብለዋል።
ከጎረቤት ሀገራት ጋር በድንበር አካባቢ የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ወዳጅነትንና ወንድማማችነትን ባከበረ መልኩ መፍትሄ ለማበጀት እየተሠራ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ በወደብ አጠቃቀምና መሰል የዲፕሎማሲ ተግባራት ላይ ስኬታማ ሥራዎች ተከናውኗል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ÷ ሚኒስቴሩ በአስቸጋሪ ጊዜያት የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም ለማሳወቅ ያደረገውን ጥረት አድንቀዋል።
የሀገርን ጥቅም ባስከበረ መልኩ ችግሮች እንዲፈቱ የሚያደርገው ጥረትም መልካም ጅማሮ መሆኑን ጠቅሰው÷ የሀገር ገጽታ ግንባታ፣ የንግድ፣ ልማትና ኢንቨስትመንት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!