Fana: At a Speed of Life!

የኩላሊት እና ሽንት ቧንቧ ጠጠር ሕክምና

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠጠር ሕመም በዋናነት በኩላሊት፣ ኩላሊትና የሽንት ፊኛን በሚያገናኘው የሽንት ቱቦ እና በሽንት ፊኛ ላይ ይከሰታል።

በዐይን (መሬት ላይ) እንደሚታየው ዓይነት ጠጠር በኩላሊት ውስጥ ሊፈጠር እንደሚችልም ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ለጠጠር ሕመም አጋላጭ ከሚባሉ መንስኤዎች መካከል፥ የኩላሊት ሥራ ስኬታማ አለመሆን፣ በቂ ውኃ አለመጠጣት፣ የሽንት መውጫ ቱቦ ክፍት አለመሆን (በተለያየ ምክንያት መዘጋት)፣ ጨው የበዛበት ምግብ እንዲሁም ሥጋ እና እንቁላል አዘውትሮ መጠቀም በዋናነት ይጠቀሳሉ።

ምንም እንኳን እንደጠጠር ዓይነቶቹ ሊወሰን ቢችልም በአብዛኛው፥ ወተትና የወተት ተዋፅዖዎችን ጨምሮ አትክልትና ፍራፍሬ ማዘውተርን ባለሙያወች ይመክራሉ።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ሕክምና ክፍል የኩላሊት ሰብ ስፔሻሊስት ዶክተር ቢኒያም ግርማ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የሕመም ምልክቶቹ ጠጠሩ እንደተከሰተበት ቦታ እንደሚለያይ ይገልጻሉ።

ለአብነትም ኩላሊት እና የላይኛው ቱቦ ላይ ከተከሰተ፥ በጎን የሰውነት ክፍል (ኩላሊቱ ያለበት ቦታ) ላይ እንዲሁም ከጎን ወረድ ብሎ እስከ ዘር ፍሬ ድረስ ከቀላል እስከ ከባድ የሕመም ስሜት ይኖራል ይላሉ።

አንዳንድ ጊዜ ጠጠሩ ከሽንት ጋር የሚወጣበት ሁኔታ እና ሽንት ደም የሚመስልበት አጋጣሚ እንዳለም ጠቁመዋል።

በሽንት ፊኛ ላይ የሚከሰት ጠጠር ደግሞ፥ ከእምብርት ወደታች ያዝ ለቀቅ የሚያደርግ የሕመም ስሜት እንዳለው፣ በሚሸኑበት ጊዜ ደም የሚመስል ፈሳሽ ሊታይ እንደሚችል እና ከሽንት ጋር ጠጠር የሚታይበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቁመዋል።

አንዳንድ ጊዜ ምልክት ላይኖረው እንደሚችል ጠቅሰው፥ በምርመራ (በአልትራሳውንድ) ግን የሕመሙ መኖር ይታወቃል ይላሉ።

በኩላሊት፣ በሽንት ቱቦ እንዲሁም በሽንት ፊኛ ላይ የሚከሰት የጠጠር ሕመም ዓይነት እንዳላቸው እና አብዛኛዎቹም ከካልሺየም ጋር ሊገናኙም ሆነ ላይገናኙ እንደሚችሉም ነው የሚናገሩት።

ለማንኛውም የጠጠር ሕመም ዓይነቶች የሚሠራ ‘አጠቃላይ ሕክምና’ የሚባል እንዳለም አስረድተዋል፡፡

የመጀመሪያው፥ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከሦስት ሊትር በላይ ውኃ መጠጣት ሲሆን÷በተለይም ለኩላሊት ጠጠር ተጋላጭ የሆኑ፣ በቤተሰብ ጠጠር ያለባቸው ሰዎች እንዲሁም ጠጠር የነበረባቸውና የዳኑ ውኃ በብዛት መጠጣት አለባቸው ብለዋል።

በእርግጥ ማንኛውም ሰው ከ2 ነጥብ 5 እስከ 3 ሊትር ውኃ እንዲጠጣ ይበረታታል ነው ያሉት።

ሌላኛው ሕክምና አመጋገብ ላይ ጨው መቀነስ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ቢኒያም ÷ ጨው የሚያበዙ ሰዎች ለጠጠር ሕመም የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ሥጋ እና እንቁላልን መቀነስ፤ አትክልትና ፍራፍሬን ማዘውተር ጠጠርን ለመከላከል ብሎም ለማከም እንደሚያግዝ አመላክተዋል።

ከላይ ከተጠቀሱት አጠቃላይ ሕክምናዎች ባሻገር፥ ምርመራን መሰረት አድርገው ለእያንዳንዱ የጠጠር ዓይነቶች የሚሰጡ ሕክምናዎች መኖራቸውንም አስታውቀዋል።

ጠጠር አንድ ጊዜ ከተፈጠረ ሊደጋገም እንደሚችል፤ ከተደጋገመ ደግሞ ኩላሊትን ሊጎዳ እንደሚችል ተናግረዋል።

ከዚያም ለኢንፌክሽን ሊያጋልጥ ብሎም አንዳንድ ጊዜ ኩላሊትን በቀዶ ጥገና እስከማስውጣት ይደርሳል ይላሉ ባለሙያው።

በመሆኑም የጠጠር ሕመም ከባድ መሆኑን በመገንዘብ ሕብረተሰቡ ለመከላከሉ ትኩረት እንዲሰጥ፤ ከተከሰተም ምርመራ በማድረግ በወቅቱ ሕክምና ሊያደርግ እንደሚገባ ዶክተር ቢኒያም ግርማ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.