ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እየተወያዩ ነው
ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ÷እንደሀገር የሚያወጣን በብሔር አጥር ውስጥ ተነጣጥለን ሳይሆን ሚዛናዊ ሆነን በኢትዮጵያዊነት ስነ ልቦና በጋራ ስንቆም ነው ብለዋል።
በአብሮነት ስሜት በጋራ ካልተነሳን ሀገራዊ አንድነትን መገንባት አንችልም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ጠንካራ ሀገር ለመገንባትና ሰላማችን ለማረጋገጥ የአብሮነት እሴቶችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
የመንግሥት ቀዳሚው ሚና የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ነው፤ ሰላም የሚገነባውም በህዝብ ልብ ውስጥ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
መንግሥት የዜጎችን ሰላም ለማረጋገጥ በሚያደርገው ሒደት ሁሉም ህዝብ ተሳታፊ መሆን እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡ፡፡
በጅምላ መፈራረጅ ችግሮቻችንን ያወሳስባል እንጂ ለውጥ አያመጣም፤ ሀገርንም አይገነባም፤ የሚዛናዊ የፖለቲካ ስርዓት ለመገንባት መቻቻልና መደማመጥ አለብን ብለዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ ÷በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች መነሻቸው ከውስጥም ከውጭም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚመኙ ኃይሎች መሆኑን ገልጸዋል።
አሸባሪው ሸኔ የኢትዮጵያ ጠላት ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ አሸባሪው ሸኔ ባለበት አካባቢ በሰላም የሚኖር ህዝብ የለም፤ ሲፈልግ ዘርን መሰረት አድረጎ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የፖለቲካ ውግንናውን መሰረት አድርጎ ንጹሃን የሚጨፈጭፍ የሁላችንም ጠላት በመሆኑ በጋራ ልንተባበር ይገባል ብለዋል።