Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በግማሽ ዓመቱ 13 ቢሊየን ብር አተረፈ

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በግማሽ ዓመቱ 13 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከጥር 16 እስከ 19 ቀን 2015 ዓ.ም የ2015 ግማሽ የበጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ጉባኤ ተከትሎ በዛሬው እለት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በሰጡት መግለጫም፥ አጠቃላይ የባንኩ ሀብት 1 ነጥብ 2 ትሪሊየን ብር መድረሱን ገልጸዋል።

ባንኩ ባለፉት ስድስት ወራት 55 አዳዲስ ቅርንጫፎችን የከፈተ ሲሆን ፥ የቅርንጫፎቹን ቁጥርንም 1 ሺህ 879 ማድረሱም ነው የተገለጸው፡፡

በግማሽ ዓመቱ 88 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ብር 978 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር መድረሱን ይፋ አድርገዋል።

2 ነጥብ 2 ሚሊየን አዲስ ደንበኞችን የቁጠባ ሒሳብ በማስከፈትም ባንኩ የደንበኞቹን ቁጥር ወደ 38 ነጥብ 1 ሚሊየን ማሳደጉ ነው የተመለከተው።

በግማሽ ዓመቱ በባንኩ የዲጂታል አገልግሎት አማራጮች አማካኝነት ከ1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር በላይ ክፍያዎች ተፈፅመዋል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

ይህም ዲጂታል ሥርዓቱ የጥሬ ገንዘብ አጠቃቀምን በመተካት ከአጠቃላይ ክፍያዎች የ39 ነጥብ 3 ከመቶ ድርሻ እንዲይዝ አድርጓል ብለዋል።

በሜሮን ሙሉጌታ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.