Fana: At a Speed of Life!

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ በኢትዮጵያ ከጃፓን አምባሳደር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ በኢትዮጵያ ከጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ሚኒስትሯ በሃገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሁለት ዝግጅትና ይዘት ከአንደኛው የቀጠለና የሃገሪቱን ቀዳሚ የኢኮኖሚ እድገት ፍላጎቶችና መሰረቶች ታሳቢ አድርጎ በመንግስት እየተዘጋጀ መሆኑን አብራርተዋል።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ መንግስት እያከናወናቸው ያሉ ልዩ ልዩ ተግባራትን በመጥቀስም በመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ዙሪያ መንግስት ከልማት አጋሮች ጋር በጋራ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በግብርና፣ በኢነርጂ በትምህርት፣ በጤና፣ በኢንዱስትሪ ልማት፣ በፋይናንስና በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፎች የግል ዘርፉን ቀዳሚ ተዋናይ ለማድረግ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የጃፓን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያላቸው ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ኤምባሲው ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያና ጃፓን የረዥም ጊዜ ወዳጅነት ያላቸው ሃገራ መሆናቸውን የጠቀሱት በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በበኩላቸው÷ የተተገበረው ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የሃገሪቱን እድገት ለማፋጠን ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።

ጃፓን የኢትዮጵያን ልማት ለማገዝ ምንጊዜም ዝግጁ ናት ማለታቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.