የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል ከ15 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል ከ15 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለፀ ፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ÷ በ2015 ዓ.ም በጀት አመት በመጀመሪያው አጋማሽ በኢትዮጵያ 2 ሺህ 145 የሳይበር ጥቃቶች እና የጥቃት ሙከራዎች ተፈፅመዋል፡፡
ከእነዚህ መካከል 2 ሺህ 49 ምላሽ የተሰጠባቸው እና የተቀሩት በሂደት ላይ እንዳሉ ጠቅሰው በመንፈቅ ዓመቱ የሳይበር ጥቃት ሙከራን የመመከት አፈፃፀም 91 ነጥብ 5 ከመቶ ማድረስ መቻሉን መናገራቸውን ከአስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የተሞከሩ ጥቃቶች ቢደርሱ የመሰረተ-ልማቶችን ማቋረጥ፤ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ለተወሰኑ ጊዜያት በማስተጓጎል ስራዎች እንዳይሰሩ በማድረግ፣ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ገቢ ያስተጓጉል እንደነበር ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም የዳታዎች መሰረቅ እና መጥፋት፤ ዳታዎችን በመመስጠር የቤዛ ክፍያ ገንዘብ መጠየቅ፤ የግንኙነትን መንገዶችን በመጥለፍ እና የክፍያን መንገድ በመጠቀም ገንዘብን በማጭበርበር እና በመውሰድ ጉዳት ይደርስ ነበር ብለዋል በመግለጫቸው፡፡
የሳይበር ጥቃት ኢላማ የተደረጉ ተቋማት አብዛኛዎቹ ትኩረታቸዉን በባንኮችና ፋይናንስ ተቋማት ላይ ማድረጋቸዉን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ የፀጥታ እና ደህንነት ተቋማት፣ ሚዲያ ተቋማት፣ ቁልፍ የመንግስት ተቋማት ፣ ሚኒስቴር መስሪያቤቶች ፣የክልል ቢሮዎች ፣ የህክምና እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥቃት ዒላማዎች እንደነበሩ አንስተዋል፡፡
በተያያዘም በተለያዩ ዘርፎች በሚገኙ 64 ተቋማት (27 የመንግስት እና 37 የግል) በተደረገ የተጋላጭነት ዳሰሳ ከተደረገባቸው የዌብ፣ የኔትዎርክ መሰረተ ልማት፣ የሞባይል መተግበሪያዎችን ጨምሮ በተለያዩ መሰረተ ልማቶች 340 የሳይበር ደህንነት የተጋላጭነትን የአደጋ ደረጃ ክፍተት መገኘቱን እና መድፈን መቻሉን አብራርተዋል።
እንደ አጠቃላይ አስተዳደሩ የሳይበር ጥቃቶችን በመከላከል ሀገሪቱ ላይ ሊደርስ የሚችል 15 ቢሊየን ብር ከኪሳራ ማዳን ተችሏል ተብሏል፡፡