Fana: At a Speed of Life!

የኑሮ ውድነት ችግርን የማቃለል ተግባር በቀጣይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል – የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዜጎች መሰረታዊ ጥያቄ የሆነውን የኑሮ ውድነት ችግር የማቃለል ተግባር በቀጣይም በልዩ ትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው  2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ÷የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርን የ2015 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ÷ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

የውጭ ምንዛሬ በመመደብ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ድፍድፍ ዘይት በመቅረቡ ግብዓቱን ተጠቅመው ያመረቱት ከ69 ሚሊየን ሊትር በላይ ዘይት ለሕብረተሰቡ መሰራጨቱን ጠቅሰዋል።

”በስድስት ወራት ከ1 ነጥብ 67 ሚሊየን ኩንታል በላይ ስኳር ለማቅረብ ዕቅድ ተይዞ በተለያዩ ምክንያቶች 445 ሺህ 532 ኩንታል መቅረቡንም ገልጸዋል።

ለዚህም ከውጭ በግዥ እንዲገባ የተፈቀደው 2 ሚሊየን ኩንታል ስኳር በዓለም የገበያ ዋጋ መናር ሳቢያ ግዥው መጓተቱ አንዱ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

መንግሥት መሰረታዊ ሸቀጦች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በፈቀደው መሰረት 47 ነጥብ 9 ሚሊየን ሊትር ዘይት መግባቱን ጠቅሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል ሩዝ እንዲሁም የተለያዩ ሸቀጦችን በማስገባት ዋጋ ለማረጋጋት ጥረት ስለመደረጉ ለምክር ቤቱ አባላት አብራርተዋል።

የኑሮ ውድነቱን የሚያባብሱ ሕገ-ወጥ ደላሎች፣ የንግድ ድርጅቶችና ምርት የሚሸሽጉ አካላት ላይ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ከወጪ ንግድ ባለፉት ስድስት ወራት 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ገቢ እንደተገኘ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አሻ ያህያ÷ሚኒስቴሩ  ህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን መከላከል እንዲሁም የኑሮ ውድነቱን የሚያቃልሉ ተጨማሪ ስራዎችን በቀጣይ ማከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.