Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ባለፉት 6 ወራት 37 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሥድሥት ወራት 37 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡
 
የቢሮው ሃላፊ መስከረም ደበበ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በተያዘው በጀት ዓመት ከመደበኛ ግብር ከፋዮች እና መዘጋጃ ቤት አገልሎት 71 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡
 
የታቀደውን እቅድ ለማሳካትም የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እና ቀልጣፋ አሰራሮችን በመዘርጋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
 
ባለፉት ሥድሥት ወራትም 38 ነጥብ 51 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 37 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አንስተዋል፡፡
 
ገቢው ከ463 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች የተገኘ መሆኑን ጠቁመው÷ በዚህም የእቅዱን 97 ነጥብ 3 በመቶ ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት ፡፡
 
ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ እንዲከፍሉም ቢሮው አስፈላጊውን ቅስቀሳ እና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ማከናወኑን ጠቁመዋል፡፡
 
በሌላ በኩል ደረሰኝ የማይከፍሉ ህገ ወጥ ነጋዴዎች በህጋዊ መልኩ ተመዝግበው አስፈላጊውን ግብር እንዲከፍሉ ስራዎች መሰራታቸውንም አስረድተዋል፡፡
 
ሀሰተኛ ደረሰኝ ማቅረብ፣ ያለ ደረሰኝ አገልግሎት እና እቃ መሸጥ እንዲሁም የጸጥታ ችግር ባለፉት ሥድሥት ወራት የተስተዋሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አንስተዋል።
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.