እስራኤል እና ሱዳን የሰላም ስምምነት ሊፈራረሙ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአረብ- እስራኤል ግጭት ምክንያት ግንኙነታቸው ሻክሮ የቆየው እስራኤል እና ሱዳን የሰላም ስምምነት ሊፈራረሙ መሆኑ ተሰማ፡፡
የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሊ ኮኸን እና ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎች ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀ መንበር አብዱል ፈታ አልቡርሃን ጋር በካርቱም ውይይት አድርገዋል፡፡
የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሊ ኮኸን ውይይቱን አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ÷ እስራኤል እና ሱዳን የሰላም ስምምነት ለመፈራረም መወሰናቸውን አመላክተዋል፡፡
ለሱዳናውያን የሰላም ስምምነት ረቂቅ ሃሳብ ማቅረባቸውን የገለፁት ኮኸን ስምምነቱ በሱዳን የሰቪል መንግስት ከተመሰረተ በኋላ የሚፈረም መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ስምምነቱ በዚህ አመት እንደሚፈረም የጠቆሙት ሚኒስትሩ እስራኤል ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች፣ ባህሬን እና ሞሮኮ ቀጥሎ የምትደርሰው የሰላም ስምምነት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የስምምነት ውሳኔው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በፍልስጤም የሚደርስባቸውን ትንኮሳ እና ከሀገሪቱ የፍትህ ስርዓት ማሻሻል ጋር ተያይዞ የተነሳባቸውን ህዝባዊ ቁጣ ያስታግሳል ነው የተባለው፡፡
በተመሳሳይ ስምምነቱ ሱዳን ከዩናይትድ ስቴትስ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶችን ጨምሮ ከሌሎች ሀገራት የገንዘብ እርዳታ እንድታገኝ ሊያደርጋት እንደሚችልም ነው የተነገረው።
ይሁን እንጂ ሱዳን በህዝባዊ ሰልፈኞች እና በሀገሪቱ ወታደራዊ ሀይሎች መካከል ባለው የፖለቲካ አለመግባባት አሁንም ውጥረት ውስጥ ትገኛለች መባሉን ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡