Fana: At a Speed of Life!

28ኛው የጉሚ በለል የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ፅ/ቤት አዘጋጅነት የሚካሄደው የጉሚ በለል ውይይት መድረክ “ህገ ወጥ ንግድን እና ኮንትሮባንድን መከላከል የዜግነት ግዴታ ነው” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል።

በውይይት መድረኩ ላይ የኢፌዴሪ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና ባለ ድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የንግድ ህግና ደንቦችን በመተላለፍ የሚፈጸሙ ህገ-ወጥ ንግድ፣ ኮንትሮባንድ እና የኢኮኖሚ አሻጥሮች ህጋዊ ለሆነው የግብይት ሥርዓት ፈተና ከመሆን ባለፈም ለሰላም መደፍረስ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በማዳከም ረገድ ትልቅ ተግዳሮት መሆናቸው በመድረኩ ተነስቷል።

ህገ ወጥነቱ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ በማሳጣት፣ የኑሮውድነትን በማባባስ እና የሀገርን ሀብት ለጎረቤት ሀገራት ሲሳይ በማድረግ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

በክልሉ ባለፉት 6 ወራት በተሰራው ስራ ለ2 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች ግንዛቤ መፈጠሩን፣ 521 ሚሊየን ብር የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ምርቶችን መቆጣጠር መቻሉን ፣ 869 ህገወጥ ንግድ የሚያካሂዱ ሱቆች እና ህገወጥ ምርቶችን የሚጭኑ ከ100 በላይ ተሽከርካሪዎችን መቆጣጠር መቻሉ ተጠቅሷል፡፡

ውይይቱ ህገወጥ ንግድ በሀገር ላይ የሚያስከትለውን ሁለንተናዊ ጉዳት ለመቀነስ እና ለመከላከል የሚያስችል ግንዛቤን በመፍጠር የህዝብ ተሳታፎን ለማሳደግ ያለመ ነው ተብሏል።

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.