Fana: At a Speed of Life!

የአንድ ማህበረሰብ ባህል፣ እሴትና ግብረ ገብነት እንዲጠበቅ ባህልና እሴቶቹን ለትውልድ ማስተማር ይገባል- ከንቲባ አዳነች

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአንድ ማህበረሰብ ባህል፣ እሴትና ግብረ ገብነት እንዲጠበቅ ባህልና እሴቶቹን ለትውልድ ማስተማር ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

14ኛው ከተማ ዓቀፍ የባህል ፌስቲቫል “ባህሎቻችን የአንድነታችን ካስማ!” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመርሐ ግብሩ የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ ባህል የአንድ ማህበረሰብ ማንነት የሚቀዳበት እንዲሁም አንድ ማህበረሰብ ከሌላው ማህበረሰብ ትስስር የሚፈጥርበት ጠንካራ ገመድ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የቱባ ባህሎች እናት ፤ በብዝሃ ማንነት፣ ባህል የተገነባች ጠንካራ ሀገር ናት ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የብዝሃ ማንነትና ባህሎች መገለጫ የሆነቸውን አዲስ አበባ በውስጧ የያዛቸውን ውብ ባህላዊ እሴቶች ለሥራ ዕድል እና ለገቢ ማግኛ አድርገን አዳብረን ልንጠቀማቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው÷ ብዝሃ ባህልና ቋንቋዎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ማንነታቸውን ጠብቀው ተደጋግፈውና ተሳስረው እንዲኖሩ ያስቻሉ አኩሪ ቅርሶች ናቸው ብለዋል።

በሁሉም የኢትዮጰያ ጓዳዎች እጅግ ውብ የሆኑ ቱባ ባህሎች አሉን ያሉት ሚኒስትሩ÷ ባህላዊ የእርቅ ፣ የዳኝነት ስርዓት፣ አቅመደካሞችን በደቦ ማገዝ፣ የተራበን ማብላት፣ አንዳችን በአንዳችን የመቆም ድንቅ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ናቸው ሲሉም አንስተዋል፡፡

አዲስ አበባ የብዝሃ ብሔር፣ ባህል፣ ስነ ጥበብ፣ ኪነጥበብ የያዘች ከተማ መሆኗን ጠቁመው÷ የከተማዋን እድገት እየቀየሩ ያሉ ፓርኮች፣ መናፈሻዎች፣ የመዝናኛ ቦታዎች ግንባታ ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

ብርቅ እና ውብ ባህሎቻችን በመጤ ባህሎች እንዳይሽርሽሩ መንከበከብና መጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊሒሩት ካሳው÷ የባህል ፌስቲቫሉ በርካታ ውብ ባህሎቻችን በአንድ ቦታ ላይ ተሰብሰባው የሚታዩበት በመሆኑ የመዲናዋ ነዋሪዎች መጥተው እንዲጉበኙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.