Fana: At a Speed of Life!

ከ410 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር እንዲሸሽ አድርገዋል የተባሉ ሰባት ግለሰቦች በሙስና ተከሰሱ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 26 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ410 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር እንዲሸሽ አድርገዋል የተባሉ አራት የጉሙሩክ ሰራተኞችና ሦሥት አስመጪ ነጋዴዎች በሙስና ወንጀል ተከሰሱ።

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾች አጠቃላይ ሰባት ሲሆኑ የጉሙሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች የሆኑት ምትኩ አበባው፣ ወተቱ አበበ ፣ ሊቁ ዘኮነ አለሙ እና ቤተልሔም ንጉሴ እንዲሁም አስመጪ ነጋዴዎች ናቸው የተባሉት ሮዛ ደፎ ቱሪ፣ ዮናስ ከበደ ደስታ እና ወንደሰን ተምትም አደራ ናቸው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ አጠቃላይ ተደራራቢ ሰባት የሙስና ወንጀል ክሶችን አቅርቦባቸዋል።

ከአንደኛ እስከ አራተኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች በጉሙሩክ ኮሚሽን ሲሰሩ ከ4ኛ እስከ 7ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ነጋዴዎች 410 ሺህ 820 የአሜሪካ ዶላር በተለያየ ጊዜ ከውጭ ይዘውት የገቡት ነው በማለት እና ዲክሌር በማድረግ ከነጋዴዎቹ ጋር በመመሳጠር ሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ በማሳጣትና ጉዳት በማድረስ ተደራራቢ በሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ቀሪዎቹ ነጋዴ ተከሳሾች ደግሞ የተጠቀሰውን የአሜሪካ ዶላር በማሸሽ እና በተወሰኑ ዶላሮች ደግሞ እቃ በመግዛት በሀገሪቱ ላይ ጉዳት በማድረስ ሙስና ወንጀል እና በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ከ3ኛ እስከ 7ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች ከሰዓት በኋላ ችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ ክሱ በንባብ ተሰምቷል።

ፍርድ ቤቱ ቀሪ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ፖሊስ መጥሪያ እንዲያደርስና በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት የቀረቡ ተከሳሾች ግን የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለየካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.