Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሩሲያ የፓርላማ አባላትን በምክር ቤቱ ተቀብሎ ያነጋገረ ሲሆን፥ ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ የኢትዮጵያ-ሩሲያ ሁለትዮሽ ግንኙነት በርካታ ዘመናትን የተሻገረ ታሪካዊ በመሆኑ አሁን ላይ ይህንን ይበልጥ ለማጠናከር በምክር ቤቱ በኩል የኢትዮ-ሩሲያ ፓርላማ ቡድን በማቋቋም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሰብሳቢው አክለውም ሩሲያ ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው በርካታ ፈታኝ ወቅትና ተግዳሮቶች፤ የሰሜኑን ጦርነት ጨምሮ ከኢትዮጵያ ጎን በመሆን በተለያዩ የዓለም አቀፍ መድረኮች ላሳየችው አጋርነት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ መሀዲ በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል ረጅም ጊዜ የቆየውን ግንኙነት በማጠናከር፥ በሁለቱ ሀገራት ላይ የሚከሰቱ ተግዳሮቶች ተመሳሳይነት ያላቸው በመሆናቸው ይህንን ለመፍታት ሁሉን አቀፍ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

በሩሲያ የፓርላማ አባል የፓርላሜንታዊ ቡድን አስተባባሪና ምክትል ግዛት አስተዳዳሪ ኒኮላይ ቪ ኖቪቺኮቭ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የሰሜኑ ጦርነት በሰላም እንዲጠናቀቅ የወሰደውን እርምጃ አድንቀው ሀገራቸው ሩሲያም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንደምታከብር ተናግረዋል፡፡

ኒኮላይ ቪ ኖቪቺኮቭ አክለውም የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትም ሀገራቸው በድንበሯ ሉዓላዊነት ለማስጠበቅና የዜጎቿን ህይወት ለመታደግ ቁርጠኛ አቋም እንዳላት ነው የገለጹት፡፡

የሩሲያ ፓርላማ ቡድን በቀጣይ ወር በሞስኮ በሚደረገው የሩሲያ-አፍሪካ ፓርላማ የጋራ ኮንፈረንስ ላይ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ ጥሪ ማድረጋቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.