Fana: At a Speed of Life!

ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች እያስመረቀ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 27 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በህክምናና ጤና እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 365 ተማሪዎች እያስመረቀ ነው፡፡

ከሚመረቁት ሰልጣኞች መካከል 234 የሚሆኑት በህክምናና ጤና ዘርፍ በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ የሠለጠኑ ሲሆኑ ቀሪዎቹ በተለያዩ የትምህርት መስኮች የሠለጠኑ ናቸው፡፡

ከዛሬ ተመራቂዎች ውስጥ ከደቡብ ሱዳን የመጡ ተማሪዎችም ይገኙበታል።

በምረቃ ስርዓቱ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የጤና ሚኒስቴር ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ብቁ የጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡

በዚህም በሀገሪቱ በህክምና እና ጤና ዘርፍ ትምህርት የሚሰጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቁጥር 37 መድረሱን ገልፀዋል፡፡

በጤናው ዘርፍ ብቁ የሠው ሃይል በማፍራት ጥሩ እምርታ ቢኖርም በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጠውን ጥምርታ ለማሟላት ብዙ መስራት ይጠይቃል ነው ያሉት።

የህክምና ሙያ እንደተከበረ እንዲቆይ በጤናው ዘርፍ የሰለጠኑ ተመራቂዎች በሰለጠኑበት ሙያ በታማኝነትና በቅንነት በማገልገል ሙያዊ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የቆላማ አካባቢዎችና መስኖ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ በበኩላቸው ተመራቂዎች አሁን ለራስና ለሀገራቸው ህልውና የሚሰሩበት ጊዜ መሆኑን ተገንዝበው ሀገራቸውን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ የለውጥ ሃዋሪያ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት አህመድ ሙስጦፋ በበኩላቸው ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀትና ሙያዊ ስነ ምግባር ተግባራዊ በማድረግ ህይወት የመታደግ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በተስፋዬ ምሬሳ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.