Fana: At a Speed of Life!

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለመሥራት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር ለመስራት የሚያስችለውን የሥምምነት ሠነድ ተፈራረመ።

ስምምነቱን በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በኩል የተቋሙ የቋንቋዎች ሥራ አሥፈፃሚ የሆኑት አቶ ሸለመ ከቤ እንዲሁም በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በኩል የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ረዳት ፕሮፌሰር አበራ ባይሳ ተፈራርመዋል።

የጋራ ሥምምነት ሠነዱ በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ በየዘርፉ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት፣ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን ወደ ተግባር ለመቀየር እንዲሁም የማኅበረሰብ ሕይወትን ለመለወጥ በትብብር መሥራት ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ለሁለንተናዊ ሀገራዊ ዕድገት በጋራ ይሠራሉ ፣ በዩኒቨርሲቲው የሚከናወኑ ማኅበረሰብ ተኮር ጉዳዮችንም በሚዲያ ተደራሽ ለማድረግ ይተባበራሉ ተብሏል፡፡

ፋና ብሮድካስትንግ ኮርፖሬት ወቅታዊ፣ አዝናኝ ፣ አስተማሪ ፣ ለኅብረተሰቡ ሕይወት ቅርብ የሆኑ፣ ለውጥ የሚያመጡ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ መረጃዎችን በ12 ኤፍኤሞች፣ በሀገር አቀፍ ሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን እና በዲጂታል ሚዲያ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ቋንዎች በፍጥነትና በጥራት የሚያደርስ በመሆኑ፣ ይህ አቅም ለዩኒቨርሲቲው ተጨማሪ ጉልበት እንደሚሆን አቶ ሸለመ ከቤ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ገልፀዋል።

ዩኒቨርሲቲዉ በተማሪዎች አገልግሎት፣ በትምህርት ልኅቀት፣ በማኅበረሰብ ዓቀፍ የልማት ሥራዎች እና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ሥራዎች የሚያስተዋውቅበት ምኅዳር እንደሚሆንም ተናግረዋል።

ፋና የራሱን የሚዲያ አውታሮች ስቱዲዮ እና ማሰራጫዎች በራሱ ብቁ ባለሙያዎች የገነባ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

በማኅበረሰብ ሬዲዮ ዘርፍ ፋናብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የድሬ ደዋ ዩኒቨርሲቲ፣ የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ፣ የስልጤ ማኅበረሰብ እና የአርጎባን ገንብቶ ያቋቋመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ስቱዲዮ ግንባታንም በፋና መካሄዱን አንስተዋል፡፡

የሌሎች ተቋማትን የማኅበረ-ሰብ ሬዲዮ ግንባታም ለማከናወን ተቋሙ በሥራ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ፋና በሚሰራቸው የምርምርና የሥልጠና ዘርፎችም ÷ ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተቀናጅቶ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ረዳት ፕሮፌሰር አበራ ባይሳ በበኩላቸው ÷ ተቋማቸው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱንና በቀጣይም ኅብረተሰብ ተኮር ሥራዎችን በጋራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር የዩንቨርሲቲውን ገፅታ ለኅብረተሰቡ ለማስተዋወቅ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በበርካታ ዘርፎች ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱንም አንስተዋል፡፡

የጋራ ስምምነቱ ሁለቱን ተቋማት ይበልጥ የሚያቀራርብ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ ከኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን፣ ከኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የስምምነት ሠነድ ተፈራርሟል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.