የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል ከ2 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎች ዳግም የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሆኑ

By Mikias Ayele

February 04, 2023

አዲስ አበባ ፣ ጥር 27 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ውድመት ደርሶባቸው በነበሩ የውሃ ተቋማት ላይ በተደረገው ጥገና ከ2 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎች ዳግም የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡

የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወንዳጥር መኮንን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት÷ በክልሉ በጦርነቱ ምክንያት በደረሰው የውሃ ተቋማት ውድመት ከ4 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎች በውሃ አቅርቦት ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡

በዘጠኝ ዞኖች የወደሙ ከ1 ሺህ 429 በላይ የውሃ ተቋማትን መልሶ ስራ ለማስጀመር 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ነው ሃላፊው የገለፁት።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው÷ በክልሉ ውድመት የደረሰባቸውን የውሃ መሰረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ በተሰራ የጥገና ስራም የተወሰኑ የውሃ መሰረተ ልማቶች ተጠግነው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በሰሎሞን ይታየው