Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን የሃይል ትስስር ለማጠናከር የበኩሏን ሚና እንደምትወጣ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኡጋንዳ ካምፓላ የተካሄደው 16ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የሃይል ትስስር የሚኒስትሮች ስብሰባ በአራት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡

በመድረኩ ኢትዮጵያን ጨምሮ የ13 አባል ሀገራት የኤሌክትሪክ ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለሙያዎች እንዲሁም የልማት አጋሮች ተሳትፈዋል፡፡

ተሳታፊቹ ለሁለት ቀናት ተሰብስበው ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ መሰረት የሚኒስትሮቹ ስብሰባ በአራት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማሳለፉ ተገልጿል።

በመጀመሪያ የሃይል ትስስር ተቋሙን ለረጅም ዓመታት ያገለገሉት ታንዛኒያዊው ጄነራል ሴክሬታሪ ኢ/ር ለቢ ቻንጉላ በመተካት በውድድር ከኬንያ አሸናፊ የሆኑትን የኢ/ር ጀምስ ካራሪ ዋሆጎን የጀነራል ሴክሬታሪነት ምርጫ አጽድቋል።

በመቀጠልም በገለልተኝነት የሃይል ትስስር ተቋሙን የሚቆጣጠረው የሬጉላቶሪ ቦርድ መቀመጫ በካምፓላ ኡጋንዳ እንዲሆን ውይይት ተካሂዶበት እንዲፀድቅ ተደርጓል።

በተጨማሪም የሁለትሽ የሃይል ሽያጭ ፍሬም ወርክ ስምምነት ጥናትና ከዚህ በፊት በሀገራት መካከል የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ የማሻሻል ሥራ በመጪው ሰኔ ወር በሚደረገው አስቸኳይ ስብሰባ አይቶ ለመወሰን ስምምነት ላይ መደረሱ ተመላክቷል፡፡

በስብሰባው ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ ተሳትፈዋል፡፡

ኢንጂነር ሱልጣን የተደረገው የሚኒስትሮች ስብሰባና የፀደቁት የውሳኔ ሃሳቦች በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የሃይል ትስስር የበለጠ የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

ሁሉም ሀገራት ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ በትብብር እንዲሰሩ የጠየቁት ሚኒስትር ዴታው÷ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የሃይል ትስስሩን ለማጠናከር የበኩሉዋን ሚና እንደምትወጣ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.