Fana: At a Speed of Life!

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኮሮናን ለመዋጋት ለኢትዮጵያ በገንዘብና በዓይነት ያደረገትን ድጋፍ ተቀበሉ

 

አዲስ አበባ፣መጋቢት 29፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኮሮናን ለመዋጋት ለኢትዮጵያ በገንዘብ እና በዓይነት ያደረጉትን ድጋፍ ተቀበሉ።

የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አገር በቀል ግበረ ሰናይ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ኮሮናን ለመወጋት እያደረገች ያለውን ጥረት ለማገዝ  የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠላቸው ተገልጿል፡፡

ድርጅቶቹ  ለኢትዮጵያ በገንዘብ እና በአይነት ያደረጉትን ድጋፍ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው  መቀበላቸው ነው የተገለጸው፡፡

ድጋፍ ካደረጉት ክልላዊ ድርጅቶች መካከል የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት /አጋድ/ ሰራተኞች ከደሞዛቸው በማዋጣት 100 ሺህ የአሜሪካን ዶላር  ማበርከታቸው ተገልጿል፡፡

ድጋፉን ያስረከቡት የኢጋድ ሴኩሪቲ ሴክተር ፕሮግራም ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ ÷ሰራተኞች ከደሞዛቸው በማዋጣት ለሁሉም የኢጋድ አባል አገራት ተመሳሳይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ከኢጋድ ድጋፍ በተጨማሪ  በርካታ የሲቪል ማህበራት ኤጄንሲዎችም ዛሬ ድጋፋቸውን  ማስረከባቸው ተገልጿል፡፡

ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ 1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር፣  ተስፋ ድርጅት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ በአይነት ፣አማራ መልሶ መቋቋም እና ልማት ድርጅት /አመልድ/ 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም  ቫሶ የተባለ ግብረሰናይ ድርጅት 1ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር፣ፓስ ፋይንደር ኢንተርናሽናል 541 ሺህ 808 ብር፣ አሁን ፍቅር ሁማኒቴሪያን ድርጅት 400 ሺህ ብር፣ራስ አገዝ ሴቶች ድርጅት 300 ሺህ ብር፣ ኦርጋናይዜሽን ፎር ዌል ፌር ኤንድ ዲቨሎፕመንት የ100 ሺህ ብር ድጋፍ  ማበርካታቸው ተገልጿል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኢፌዲሪ መንግስት ስም ድጋፉን የተቀበሉ ሲሆን፥ የዛሬው ድጋፍ መንግስት እያካሄደ ላለው እንቅስቃሴ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

ኮሮናን ለመዋጋት ለሚደረገው እንቅስቃሴ ዛሬ በድርጅቶቹ ለተደረገው ድጋፍ በራሳቸው እና በመንግስት ስም ምስጋና በማቅረብ በሁሉም አካላት ትብብር ኮሮና ከደቀነብን አገራዊ ችግር ለመውጣት እንደሚቻል ጽኑ እምነት እንዳላቸው መግለፃቸውን ነው ከሚኒስቴሩ ቃለ አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው።

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.