Fana: At a Speed of Life!

ህወሓት ያስረከባቸውን መሳሪያዎችና ተሽከርካሪዎች የማጓጓዝ ስራ መጀመሩን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ህወሓት ያስረከባቸውን መሳሪያዎች እና ተሽከርካሪዎችን የማንቀሳቀስ ስራ መጀመሩን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ፡፡

በፌዴራል መንግስትና በህወሓት አመራሮች መካከል ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ ላይ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሠረት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የተረከባቸው የተለያዩ ተሽከርካሪዎችና የጦር መሳሪያዎች ከቦታው መንቀሳቀስ ጀምረዋል።

ጥር 2 ቀን 2015 ዓ.ም ከመቀሌ 36 ኪሎ ሜትር ርቀት ከሚገኘው አጉላ ካምፕ የአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ ታዛቢዎች በተገኙበት ህወሓት ያስረከባቸው መሳሪያዎች ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ተተኳሾች ወደ ተዘገጀላቸው ቦታ በኮንቮይ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡

በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የሎጄስቲክስ ዋና መምሪያ ኮሎኔል ነጋ መንገሻ÷ “በተደረሠው ስምምነት መሠረት ወታደራዊ ንብረቶቹን ተረከብን ከቦታው በማንሳት ወደ ተዘጋጀው ቦታ ጉዞ ጀምረናል” ብለዋል፡፡

በቀጠናው የተሰማራው ሰራዊት አመራር ሌተናል ኮሎኔል አለሜ ታደለ በበኩላቸው÷ “ተቋማችን የሰጠንን ትዕዛዝ በሚገባ ተገንዝበን ከህወሓት አመራሮች ጋር በመነጋገር ተሽከርካሪዎችን እና መሳሪያዎችን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ መሰረት ተረክበን ለመከላከያ ሎጀስቲክስ ዋና መምሪያ አስረክበናል” ብለዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ንብረቶቹን የማጓጓዝ ስራም ተጀምሯል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.