የሀገር ውስጥ ዜና

በ6 ወራት ለውጭ ከቀረበ የኤሌክትሪክ ሽያጭ 40 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ተገኘ

By Shambel Mihret

February 05, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው ግማሽ በጀት ዓመት ለጅቡቲ እና ሱዳን ከቀረበው የኤሌክትሪክ ሽያጭ 39 ነጥብ 8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

ለውጭ ገበያ የተደረገው የኤሌክትሪክ ሽያጭ አፈጻጸምም 89 በመቶ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ለጅቡቲ ከተደረገ የኤሌክትሪክ ሽያጭ 19 ነጥብ 9 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ÷ 21 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን በተቋሙ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ተናግረዋል፡፡

ከዕቅድ በላይ 8 በመቶ ጭማሬ ማሳየቱንም ነው የጠቆሙት፡፡

ለሱዳን ከቀረበ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ደግሞ 24 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ÷ 18 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ተገኝቷል ብለዋል፡፡

ወደ ኬንያ በቅርቡ ሽያጭ መጀመሩን ጠቁመው ለተወሰነ ጊዜ በሙከራ ስለሚቆይ ትክክለኛ (መደበኛ) ሽያጩ ሲረጋገጥ ለውጭ ሀገራት ከሚቀርበው ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ከፍ እንደሚል አመላክተዋል፡፡

በሌላ በኩል ለኢትዮ ቴሌኮም፣ ለሳፋሪ ኮም እና ለዌብ ስፕሪክስ አይ ቲ ሶልዩሽን ተቋማት ኦፕቲካል ፋይበር በማከራየት 54 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ገቢ ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡

የዚህ ዘርፍ አፈጻጻምም 122 በመቶ መሆኑን ነው አቶ ሞገስ የገለጹት፡፡

በሀገር ውስጥ ደግሞ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ለከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚዎች እና ለኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የ9 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የኤሌክትሪክ ሽያጭ ለማከናወን መታቀዱን አመልክተዋል፡፡

ክንውኑም 8 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር መሆኑን እና የዕቀዱ 89 በመቶ መፈጸም መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው