Fana: At a Speed of Life!

ነገ ለሚካሔደው ሕዝበ ውሳኔ ዝግጅት መጠናቀቁን የተለያዩ ዞኖች አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ነገ ለሚካሔደው ሕዝበ ውሳኔ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የተለያዩ ዞኖች አስታውቀዋል፡፡

የጎፋ ዞን አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪና የሕዝበ ውሳኔ ተጠሪ ብርሃኑ ደቻሳ እንደገለጹት÷ ከነዋሪዎች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሴቶችና ወጣት አደረጃጀቶች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡

ነፃና ፍትሐዊ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግም ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ በዞኑ በባዋቀራቸው 329 ጣቢያዎች በእያንዳንዱ ጣቢያ ላይ በቂ ስልጠና የወሰዱ ሦስት ባለሙያዎች መመደባቸውን አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ 304 ሺህ መራጮች ተመዝግበው ነገ ድምፅ ለመሥጠት ዝግጁ መሆናቸውን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

በሣውላ፣ ባቶ እና ላሃ ማዕከላት የምርጫ ቁሳቁስ መሟላቱንም ነው ያረጋገጡት፡፡

የዞኑ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ ብርሃኑ ጅፋር በበኩላቸው÷ ነገ የሚደረገው ሕዝበ ውሳኔ በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

የዞኑ የሕዝበ ውሳኔ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት÷ ነገ ከማለዳው 12 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት ድረስ በሚካሔደው ሕዝበ ውሳኔ ነዋሪዎች ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ድምፅ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በተመሳሳይ የደቡብ ኦሞ ዞን ነገ ለሚካሔደው ሕዝበ ውሳኔ በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል፡፡

በዞኑ 301 ሺህ 324 መራጮች በ428 የምርጫ ጣቢያዎች ለመምረጥ መመዝገባቸው ተገልጿል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ንጋቱ ዳንሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ ሕዝበ ውሳኔው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን ዝግጅት ተጠናቋል።

የዞኑ ነዋሪዎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም በምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እንዲሁም በጌዴኦ  ዞን  የሚደረገው  ሕዝበ ውሳኔ  በሰላም  እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው  ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የዞኑ አስተዳደር  አስታውቋል፡፡

የዞኑ ሕዝብ ምርጫው  በሰላም  እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዮት ደምሴ ጠይቀዋል፡፡

በማቱሣላ ማቴዎስ፣ መለሰ ታደለ እና ኢብራሂም ባዲ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.