የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ክልል ነገ ሕዝበ ውሳኔ እንደሚካሔድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

By Shambel Mihret

February 05, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ነገ ሕዝበ ውሳኔ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

በክልሉ ስር በሚገኙ÷ የጋሞ፣ ጎፋ፣ ዎላይታ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶና፣ ደቡብ ኦሞ ዞኖች ሕዝበ ውሳኔ ይካሔዳል ብሏል ቦርዱ፡፡

በተጨማሪም በቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ እና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች ሕዝበ ውሳኔ እንደሚያካሂድ ነው ምርጫ ቦርድ ያስታወቀው፡፡

በሕዝበ ውሳኔው ላይ 5 ሺህ 274 የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች ይሠማራሉ መባሉን ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ቦርዱ በክልሉ ለሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ባካሄደው የመራጮች ምዝገባ÷ 3 ሚሊየን 28 ሺህ 770 ሰዎች ድምፅ ለመስጠት መመዝገባቸውንም አሳውቋል፡፡

በድምፅ መስጫ ቀን አገልግሎት ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶችን በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ማሰራጨቱንም ነው ያረጋገጠው፡፡

የቁሳቁስ ስርጭቱ የተከናወነው በ31 ማዕከላት ስር ባሉ 3 ሺህ 771 ምርጫ ጣቢያዎች መሆኑ ተገልጿል፡፡

ጣቢያዎቹም ነገ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ክፍት እንደሚሆኑ ነው ቦርዱ ያስታወቀው፡፡

መራጮች በተጠቀሰው ሰዓት ወደተመዘገቡበት ጣቢያ በመሄድ ድምፃቸውን እንዲሰጡም አሳስቧል፡፡