Fana: At a Speed of Life!

ከአውቶቡስ ተራ-18 ቁጥር ማዞሪያ-መሳለሚያ ለሚገነባው የመንገድ ፕሮጀክት ኮንዶሚኒየም ለመረጡ ተነሺዎች ቤት ተመድቧል- ኮርፖሬሽኑ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ኮርፖሬሽን ከአውቶቡስ ተራ-18ቁጥር ማዞሪያ-መሳለሚያ እየተገነባ ባለው የመንገድ ፕሮጀክት ምክንያት ተነሺ ለሆኑና ኮንዶሚኒየም ለመረጡ ሁሉም ሰዎች ቤት መመደቡን ገለፀ።

ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ የወሰን ማስከበር ሥራ እንቅፋት እንደሆነበት የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን መግለጹን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጥር 21 ቀን 2015 ዓ.ም መዘገቡ ይታወቃል፡፡

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አንዱዓለም ይጥና፥ ቁልፍ ያልተረከቡ እና ቤት ያልተመደበላቸው ተነሺዎች አሉ ማለታቸው ይታወሳል።

ከዚህ ባለፈም ኮርፖሬሽኑ ኮንዶሚኒየም የመረጡ ተነሽዎችን በአስቸኳይ ካስተናገደ እስከ አንድ ወር ሙሉ በሙሉ ለማንሣት ዝግጁ እንደሆኑ መግለጻቸውም ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አውራሪስ ከበደ በበኩላቸው፥ “የአዲስ አበባ መሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ አረጋግጦ ኮንዶሚኒየም እንዲሰጣቸው ለላከልን ሁሉም ተነሽዎች ቤት መድበናል” ብለዋል።

አንዳንድ ተነሽዎች ኮርፖሬሽኑ የመደበላቸውን ቤት ‘አንቀበልም’ ማለታቸውንም ነው የሚናገሩት።

በልማት ምክንያት ተነሽዎች እንዲስተናገዱ መመሪያ በሚያዘው መሰረት ኮርፖሬሽኑ ያሉትን ቤቶች መድቧል ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ።

ምደባው በተነሽዎቹ ምርጫ ያልተፈፀመው ኮርፖሬሽኑ የቤት እጥረት ስላለበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም ቤት ተመድቦላቸው በገንዘብ እጥረት፣ ውርስ፣ ጋብቻ እና ሌላ ምክንያት አስገዳጅ ሂደቶችን ያላጠናቀቁ እንዳሉም ነው የጠቆሙት።

ተነሽዎቹ ቤቱን ለመረከብ አስገዳጅ ሂደቶችን መቋጨት እንዳለባቸው ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል።

እንዲሁም የተመደበላቸውን ቤት ዋጋ 20 በመቶ ቅድሚያ ሲከፍሉና ቀሪውን ከባንክ ጋር ሲዋዋሉ ቁልፍ ያልተረከቡ ሰዎች ይስተናገዳሉ ተብሏል።

ቁልፍ ያልተረከቡ ሰዎች ወደ ኮርፖሬሽኑ ቢመጡ ከባንክ ጋር የማዋዋሉ ስራ በፍጥነት እንደሚፈፀምላቸው አቶ አውራሪስ አረጋግጠዋል።

በዮሐንስ ደርበው

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.