Fana: At a Speed of Life!

የጨጓራ አልሰር ምልክቶች፣ መከላከያ መንገዶችና ህክምናው

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለምዶ የጨጓራ አልሰር (Peptic ulcer disease) ወይም የጨጓራና የትንሹ አንጀት መጀመሪያ ክፍል መላጥ፣መቦርቦር ወይም መቁሰል የሚከሰተው በጨጓራ በሚመነጭ አሲድ ምክንያት ነው።

የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስቱ ዶክተር ሸምሴ ሸውሞሎ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ የጨጓራ አልሰር መከሰቻ ምክንቶችን ይጠቅሳሉ።

– ኤች-ፓይሎር የተባለ ባክቴሪያ፦ አብዛኛው ሰው የዚህ ባክቴሪያ ኢንፌክሽን ያለው ሲሆን ምንም እንኳ በዚህ ባክቴሪያ የተያዘ ሁሉ በጨጓራ አልሰር ባይጠቃም የዚህ ባክቴሪያ መኖር ለአልሰር የመጋለጥን እድልን ከፍ ያደርገዋል ይላሉ።

እንደ እሳቸው ገለፃ ይህ ባክቴሪያ የጨጓራን ግድግዳ ከአሲድ የሚከላከለውን “ሙከስ” በመቀነስና የአሲዱንም መጠን በመጨመር ጉዳት ያደርሳል።

– አንዳንድ የህመም ማስታገሻዎች፦ እንደ አስፕሪን ፣ አይቡፕሮፌንና ዳይክሎፌናክ ያሉ ነን ስቴሮይዳል ፀረ-ብግነት መድሀኒቶች ለረጅም ጊዜ ከተወሰዱ የጨጓራ አልሰር ያስከትላሉ ።

-ሲጋራ ማጨስ፣ የአልኮል መጠጥ መጠጣት ፣ ጭንቀት፣ ከባድ የአካል ጉዳት፣ ከፍተኛ ቃጠሎ፣ የጭንቅላት አደጋ፣ አደገኛ ኢንፌክሽን እና ከባድና የተወሳሰበ ቀዶ ህክምና የጨጓራ አልሰርን ሊያመጣ ይችላል ብለዋል ።

የሆድ መነፋት ስሜት፣ ማስገሳት፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ እንብርት እና ከፍ ብሎ ያለ አካባቢ ያለመመቸት ስሜትና ሌሎች የጨጓራ አልሰር ምልክቶች መሆናቸውንም ይገልጻሉ፡፡

ከአልሰር መከላከያ መንገዶች ውስጥም አንዳንድ የህመም ማስታገሻዎችን በተደጋጋሚ ያለ ሀኪም ትዕዛዝ መውሰድን ማቆም ፣የአልኮል መጠጣትና ጫት መቃምን ማስወገድ እንዲሁም ጭንቀትን ማስወገድ እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡

ምርመራዎቹም የ ኤች-ፓይሎሪ ምርመራ፣ የኢንዶስኮፒ ምርመራና ሌሎች ምርመራዎች ሊታዘዙ ይችላሉ።

በህክምና ባለሙያ ታይቶም መርፌ ፣ የአሲድ መቀነሻ የተለያዩ የሚዋጡ መድሀኒቶች፣ አሲድ ማምከኛ የሚታኘኩ መድሀኒቶች፣አሲድ ማምከኛ ሽሮፖችና ኤች-ፓይሎሪን ማጥፊያ መድሀኒቶች ይሠጣሉ፡፡

የጨጓራ አልሰር በትክክል ካልታከመም ከፍተኛ መድማት ፣መበሳትና፣ የጨጓራ መውጫ መዘጋት(ይህ አልሰሩ የትንሹ አንጀት የመጀመሪያ ክፍል ጠበሳ ፈጥሮ ከጨጓራ ወደ ትንሹ አንጀት የሚያስተላልፈው ቱቦ ሲዘጋ ይፈጠራል) ያስከትላል ነው ያሉት የህክምና ባለሙያው።

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.