Fana: At a Speed of Life!

በቱርክ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቱርክ በደረሰው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተገለፀ፡፡

እየተደረገ ባለው የነፍስ አድን ጥረትም የቱርክ ግዛቶች የመጀመሪያውን የተጎጂዎች ግምታዊ ቁጥር ይፋ አድርገዋል፡፡

ዛሬ ማለዳ በማዕከላዊ ቱርክ በደረሰ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከ70 በላይ ሰዎች ለህልፈት ሳይዳረጉ እንዳልቀረ እና በርካቶችም በፍርስራሽ ውስጥ ተቀብረዋል የሚል ስጋት እንዳለ የአር ቲ ዘገባ አመላክቷል።

የቱርክ የአደጋ ምላሽ ማዕከል÷ ሳኮም ካህራማንማራስ፣ ጋዚያንቴፕ፣ ሳንሊዩርፋ፣ ዲያርባኪር፣ አዳና፣ አድያማን፣ ማላቲያ፣ ኦስማኒዬ፣ ሃታይ እና ኪሊስ አካባቢዎች ቢያንስ 76 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን እና ሌሎች 440 መቁሰላቸውን አረጋግጧል።

በግዛቶቹ እስካሁን ቢያንስ ከ190 በላይ ህንጻዎች መውደማቸውን የየአካባቢዎቹ አስተዳዳሪዎች ገልጸዋል።

የነፍስ አድን ሰራተኞች በህይወት የተረፉ ሰዎችን ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

አደጋውን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን፥ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይፕ ኤርዶኻን ሁሉንም የነፍስ አድን አገልግሎቶችን እና የአደጋ ጊዜ የመጀመሪያ ምላሽ ሰጪዎችን በማሰባሰብ የተጎዱ ግዛቶችን ለመርዳት የሚደረጉ ጥረቶችን እያስተባበሩ መሆኑ ተጠቁሟል።

በተመሳሳይም ቱርክን ያጠቃው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ፣ ሰሜን እና ምእራብ ሶሪያን የመታ ሲሆን፣ የምስራቅ ሜዲትራኒያን አካባቢንም ማናወጡን የአልጀዚራ ዘገባ አመላክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመጀመሪያው በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 8 የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ከደረሰ ከሠዓታት በኋላ በቱርክ በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 7 ሆኖ የተመዘገበ ሌላ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በተመሳሳይ አካባቢ ተከስቷል፡፡

በዚህም ከ1 ሺህ 500 በላይ የሰዎች ሕይወት መቀጠፉን ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.