የሀገር ውስጥ ዜና

“የዓየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ” በሥርዓተ ትምህርት ተካትቶ ሊቀርብ ይገባል ተባለ

By Alemayehu Geremew

February 06, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)ኢትዮጵያ የዓየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ አሳሳቢነትን ለመግታት “የዓየር ንብረትን” በሥርዓተ ትምህርቷ ውስጥ አካታ ልትሰጥ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ሜቲዎሮሎጂ ተመራማሪ ዶክተር ቶማስ ቶሮራ÷ የዓየር ንብረት ጉዳይ ኢትዮጵያ በምግብ ምርት ራሷን ከመቻል አልፋ ለሌሎች ለመትረፍ የምታደርገውን ጥረት ይወስናል ብለዋል፡፡

ምሁሩ ዛሬ ከ“ኔት ዜሮ ሾው” ጋር የነበራቸውን ቆይታ ሲሽን ዓለምአቀፍ የዜና እና የሕዝብ ግንኙነት መረጃዎች ምንጭ አስነብቧል፡፡

የዓየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ ኢትዮጵያ ዘላቂ ግብርና እና የሀገሪቱን ብሎም የአፍሪካን የደን ሽፋን ማሳደግ ላይ እየሠራች መሆኗን ዶክተር ቶማስ አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ተፈጥሮ በታዳሽ ኃይል የበለፀገች እንድትሆን አድሏታልም ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በግብርና ላይ መመስረቱን እና አብዛኛው ኢትዮጵያዊይም በዘርፉ ላይ ተሰማርቶ እየሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ግብርና የሀገሪቷን 45 በመቶ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ገቢ እንደሚሸፍንም ነው ያነሱት፡፡

የዓየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በኢትዮጵያ ድርቅ ማስከተሉንም አመላክተዋል፡፡

በዓየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ምክንያት በዕፅዋ፣ በምግብ አዝዕርት እና በእንስሳት ላይ ጉት መድረሱንም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተከሰተው የዓየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በተወሰኑ አካባቢዎች በተለይም በእንስሳት እርባታ እና በእርሻ የሚተዳደሩትን ለምግብ አቅርቦት ብሎም ለንፁህ የመጠጥ ውኃ እጥረት እንደዳረጋቸው ገልጸዋል፡፡

በዓለማየሁ ገረመው

#Ethioia