በደቡብ ክልል በሙስና የተጠረጠሩ 49 ግለሰቦች ላይ ክስ ለመመስረት ዝግጅት ተጠናቋል
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል በተለያዩ ዘርፎች በሙስና የተጠረጠሩ 49 ግለሰቦች ላይ ክስ ለመመስረት ዝግጅት ማጠናቀቁን የክልሉ ጸረ ሙስና ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
የደቡብ ክልል ሰላምና የጸጥታ ቢሮ ሃላፊ እንዲሁም የፀረ ሙስና ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አለማየሁ ባውዲ፥ ኮሚቴው ሙስና የሚስተዋልባቸውን ወሳኝ ዘርፎች በመለየት እና እቅድ በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባቱን አንስተዋል፡፡
በእቅዱ ከዚህ በፊት በከባድ ሙስና ተጠርጥረው የነበሩ እና በተለያዩ ምክንያቶች ተደናቅፈው ለቀሩ ጉዳዮች ቅድሚያ መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ከተቋማት እና ግለሰቦች አዳዲስ የሙስና ጥቆማዎችን የመቀበል እና የማደራጀት ስራ መሰራቱን ነው የገለጹት።
እስካሁን በተከናወነ የማጣራት ስራም በአራት መዝገቦች በሙስና የተጠረጠሩ 49 ግለሰቦች ላይ ክስ ለመመስረት ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በሙሉ እንዲያዙና እና ያላቸው ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ሃብትም መታገዱን አስረድተዋል።
ግለሰቦች ከመሬት ምዝበራ፣ ከአፈር ማዳበሪያ፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ እና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተገናኘ በሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን ሰብሳቢው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ከተቋማት እና ግለሰቦች በርካታ ጥቆማዎች እየቀረቡ መሆኑን የገለጹት አቶ አለማየሁ÷ ጥቆማዎችን የመለየት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የቀረቡ መረጃዎችን ወደ ማስረጃ ለመቀየር እና አስፈላጊውን ማጣራት ለማድረግ ንዑስ ኮሚቴ ተዋቅሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ሙስና ለሀገር እድገት እና ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንቅፋት ነው ያሉት ሰብሳቢው፥ ማህበረሰቡ ጥቆማ ከማድረግ ባለፈ አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ