Fana: At a Speed of Life!

ከዔልሻዳይ የዕርዳታ ድርጅት ጋር ተያይዞ በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱት ግለሰቦች ላይ የምስክር ቃል መስማት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከዔልሻዳይ የዕርዳታ ድርጅት ጋር ተያይዞ በከባድ የሙስና ወንጀል በተከሰሱት በእነ አቶ ምትኩ ካሳ ላይ የምሥክር ቃል መስማት ተጀመረ።

የምስክር ቃል መሰማት የተጀመረው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

በተለያዩ ጊዜያት በአማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ እንዲሁም በደቡብ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ በ”ዔልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ግብረሰናይ ድርጅት” ማዕከላት ውስጥ የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ እህልና ቁሳቁሶችን ከኮሚሽኑ በመውሰድ ለተረጂዎች ሳያደርስ በመሸጥ ፣ እንዲሁም በብድርና ድጋፍ በሚል ሰበብ በመቶ ሚሊየን የሚገመት በገንዘብ መልክ ለእርዳታ ድርጅቱ ተላልፎ ተሰጥቷል ፤ ገንዘቡም ለግል ጥቅም ውሏል ፤ በሚል በተከሳሾቹ ላይ ዐቃቤ-ሕግ ነኀሴ 20 ቀን 2014 ዓ.ም በተደራራቢ የከባድ ሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

ከአጠቃላይ 13 ተከሳሾች ውስጥ የቀድሞ የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ምትኩ ካሳን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾች ብቻ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ተደርጎ ነበር።

ቀሪ ተከሳሾች ማለትም የ”ዔልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን” ዋና ዳይሬክተር የማነ ወ/ማሪያም ን ጨምሮ ሰባት ተከሳሶች በተደጋጋሚ ቀጠሮ በፖሊስ ተፈልገው እንዲቀርቡ የታዘዘ ቢሆንም ፖሊስ በአድራሻቸው ሊገኙ አለመቻላቸውን ገልጾ መልስ መስጠቱን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ እስከሚገኙ ድረስ ለጊዜው ክሳቸው እንዲቋረጥ ብይን መስጠቱ ይታወቃል።

ከዚህም በኋላ በታኅሣሥ 19 ቀን 2015 ዓ.ም በነበረ ቀጠሮ እነ አቶ ምትኩ ካሳን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾች በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የሙስና ወንጀል አልፈጸምንም በማለት የዕምነት ክኅደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ዐቃቤ-ሕግም ”ተከሳሾቹ ወንጀሉን አልፈጸምንም ያሉ በመሆኑ ምስክሮቼን አቅርቤ ለማሰማት ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ” ሲል ጠይቆ ነበር።

የምስክር ቃል ለመስማት ለዛሬ በሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት ችሎቱ ጠዋትና ከሰዓት በኋላ ተሰይሟል።

1ኛ ተከሳሽ የቀድሞ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ምትኩ ካሳ እና የአቶ ምትኩ ልጅ የሆኑት አቶ እያሱ ምትኩ ፣ የኤልሻዳይ ተራዶድዖድርጅት ንብረት ክፍል ሠራተኛ የሆኑት 11 ኛ ተከሳሽ ዮሀንስ በላይ፣ የአቶ ምትኩ ካሳ ባለቤት የሆኑት ወይዘሮ ሶፊያ ጀማል ፣ ሌላኛዋ የአቶ ምትኩ ልጅ ወይዘሮ ሚልካ ምትኩ እንዲሁም ክሳቸው ለጊዜው የተቋረጠላቸው የ12ኛ ተከሳሽ የአቶ ጌቱ አስራት ባለቤት (የትዳር አጋር) ወይዘሮ ሕይወት ከበደ ከጠበቆቻቸው ጋር ቀርበዋል።

ዐቃቤ-ሕግ በክሱ ካስቆጠራቸው አጠቃላይ 55 ምሥክሮቹ ውስጥ ጠዋት በነበረው ቀጠሮ 25 ምስክሮቹን በቀዳሚነት አቅርቦ አስመዝግቧል።

በዚህ መሰረት ፍርድ ቤቱ ከሰዓት በኋላ የዐቃቤ ሕግ ምሥክርን መስማት ጀምሯል።

የመጀመሪያው ምሥክር የኦዲተር ባለሙያ ሲሆኑ የሙያ የምሥክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

የምስክር አሰማሙ በነገው ዕለትም ይቀጥላል ተብሏል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.