አምባሳደር አየለ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ኅብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር አየለ ሊሬ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር አቀረቡ።
በዚህም ወቅት አምባሳደሩ የሹመት ደብዳቢያቸውን ከተቀበሏቸው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ውስጥ በነበራት ሚና ፣ በቀጣዩ የኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ዝግጅት ላይ እና በሌሎችም ተያያዥ የጋራ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
አምባሳደር አየለ ሊሬ፥ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር የላኩትን መልዕክትንም አድርሰዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተፈጠረው ግጭት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ላሳዩት የማያወላውል ድጋፍ እና አጋርነትም አመስግነዋል።
አምባሳደር አየለ ለኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር በፕሪቶሪያው የሠላም ሥምምነት አተገባበር ላይ ማብራሪያ እንደሰጧቸውም ነው የተጠቆመው፡፡
ስምምነቱ እና አተገባበሩ “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካ መፍትሄ” የሚለውን የኅብረቱ መርኅን በተግባር ያሳየ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ቀጣዩን የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ በብቃት ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን አስረድተዋል፡፡
ሙሳ ፋኪ ማሃማት በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ለፓን-አፍሪካ ዕውን መሆን፣ ለአኅጉራዊ ሠላም እና ደኅንነት የተጫወተችውን እንዲሁም ፅንፈኝነትን በመዋጋት የምትጫወተውን አወንታዊ ሚና አድንቀው ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-