Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ጉዳት የደረሰባቸው ሁሉንም የውሃ መሰረተ ልማቶች ስራ ለማስጀመር እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሁሉንም የውሃ መሰረተ ልማቶች በፍጥነት ዳግም ስራ ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
 
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በትግራይ ክልል 5 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎችን ዳግም የውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በትብብር እየተሰራ ነው፡፡
 
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎም በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት የደረሰባቸው የውሃ ተቋማትን ጠግኖ ዳግም አገልግሎት ለማስጀመር በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
 
በተለይም ዓድዋ፣ አክሱም፣ ሽረ፣ ሽራሮ፣ ሰለኽለኻ፣ ዓዲ ሃገራይ፣ ዓዲ ዳዕሮ፣ ዓዲ ነብሪኢድ፣ እንዳባጉና ውቕሮ ማርያምን ጨምሮ በ76 ከተሞች እና ወረዳዎች አስፈላጊው የጥገና ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡
 
በዚህም ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዜጎች ዳግም የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
 
ለዚህም ሚኒስቴሩ እስካሁን ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ውጪ ማድረጉን የገለጹት ሚኒስትሩ፥ አጋር አካላትም በርካታ ድጋፍ አማድረጋቸውን አንስተዋል።
 
በቀጣይም ሌሎች አካባቢዎች ጉዳት የደረሰባቸውን የውሃ መሰረተ ልማቶች ዳግም ስራ ለማስጀመር ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ነው የገለጹት።
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.