የአፋር ክልል ምክር ቤት 3ኛ መደበኛ ጉባኤ አዋጆችን ጨምሮ የዳኞችና የአስፈጻሚ አካላትን ሹመት አፀደቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 6ኛው የአፋር ክልል ምክር ቤት 3ኛ መደበኛ ጉባኤ አዋጆችን ጨምሮ የዳኞችና የአስፈጻሚ አካላትን ሹመት በማጽደቅ ዛሬ ተጠናቀቀ፡፡
ባለፉት ሶስት ቀናት በሰመራ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የአፋር ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ ሲመክር ቆይቶ የተለያዩ ሹመቶችን በመስጠት ዛሬ ተጠናቋል፡፡
ጉባኤው በትናንት ቀን ውሎው የክልሉን አስፈጻሚ አካላት ሪፖርትና ሁለት አጀንዳዎችን መርምሮ ያጸደቀ ሲሆን፥ በዛሬ የመጨረሻ ቀን ውሎውም የስድስት ዳኞችና የአራት አስፈጻሚ አካላትን ሹመት መርምሮ በማጽደቅ ተጠናቋል፡፡
በዚህ መሠረት አቶ አሊ መሀመድ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ፣ አቶ አብዱ ሃሰን ያዮ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ፣ አቶ አወል አብዱ አወል የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ እንዲሁም አቶ አመር ኑር የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ ሆነው ተሾመዋል፡፡
ተሻሚዎቹ በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው የተሰጣቸውን የህዝብና መንግስት ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ቃለ መሃላ መፈፀማቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡