ከአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ
ሀገራችን ኢትዮጵያ እምነቶችን ቀድመው ከተቀበሉ እና ለአለም ህዝብ አርአያ ከሆኑ ቀዳሚ ሀገራት ተርታ እንደምትሰለፍ ይታወቃል።
ልጆቿም ተከባብረውና ተቻችለው በሀገር ጉዳይ ላይ ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው እንደ አንድ ሰው ልብ በመሆን ከፈጣሪ በታች ሀገርን ከነ ክብሯ አቆይተው ለዛሬ አሸጋግረዋል። ለዚህም ውጤት በኢትዮጵያ የሚገኙ የእምነት ተቋማት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
የእምነት ተቋማት መጠናከርና ህጋዊ መሰረትን ተከትሎ እምነት ማራመድ ለሀገራዊ አንድነት መጠናከርና ለሀገር ጉዳይ ቅድሚያ ለመስጠት ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው።
ከሀገራዊ ለውጥ ማግስት ጀምሮ እንደ ሀገር መንግስት ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ተሰጥቶት ሰፊ ጥረት ካደረገባቸው ዘርፎች ውስጥ ህገመንግስታዊ መርሆዎችን በጠበቀ አኳኋን የእምነት ተቋማት እንዲጠናከሩ ሰፊ ስራ ተሰርቷል፡፡
በእምነት ተቋማት የነበሩ ልዩነቶች እንዲቀራረቡ እና አንድ ሆነው አማኞቻቸውን በተለያዩ ጎራዎች ሳይሆን በአንድ ጥላ ስር እንዲሆኑ፣ የእምነት ተቋማት ህጋዊ መሰረት ኖሯቸው እንዲደራጁ፣ ለሀገር እድገትና ብልፅግና ቀዳሚ ተሰላፊ እንዲሆኑ ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡
በእምነት ተቋማት ውስጥ ችግሮች ቢከሰቱ መፍትሄው የሚገኘው በራሳቸው ተቋማት በመሆኑ ተቋማት ችግሮቻቸውን በውስጥ አሰራር እና ህገመንግስታዊ መርሆዎችን በጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበት መንግስት ያምናል፡፡
የውስጥ ችግሮቻችንን ሁሌም አሰፍስፈው የሚጠብቁና ከዛም አልፎ የውስጥ ችግሮች እንዲነሱ ከጀርባ ሆነው የሚያራግቡ ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ የምታደርገው ጉዞ የማይመቻቸው አካላት ጊዜያዊ የሆነ ውስጣዊ ችግሮቻችን መጠቀሚያ ለማድረግ የራሳቸው የሆነ ድብቅ አጀንዳ ለማስፈጸም የሚፈልጉ ሃይሎች እንዳሉ ህዝባችን ሊያውቅ ይገባል፡፡
ከሰሞኑም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ከሃይማኖት ጉዳይነት አልፎ ችግሩን በማወሳሰብ በርካታ እኩይ ዓላማ ያላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ የፖለቲካ ኃይሎች ተቀናጅተው ኢትዮጵያን ለማዳከም ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ችግሮቻቸውን ህገ መንግስቱን መሰረት ባደረገ መልኩ በውስጣዊ አሰራር ከመፍታት ባሻገር በጋራ ያቆምናትን ሀገራችንን ለማፍረስ ሴራ ለሚሸርቡ አካላት መጠቀሚያና ማስፈፀሚያ እንዳይሆኑ ነገሮችን በአፅንኦትና በትኩረት የዛሬን ችግር ብቻ ሳይሆን ነገንም ያገናዘበ መሆን አለበት።
ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ ድብቅ አጀንዳ ያላቸው አካላት በሚፈጥሩት የሰላም እጦት፣ ሁከት፣ ረብሻ እና ብጥብጥ ሀገርን እንደሚጎዳ፣ ሀገርን ለዘርፈ ብዙ ችግሮችና አደጋዎች የሚከት ሀገራዊ ችግሩም በአገልባጩ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ቤት እንደሚያንኳኳ በማወቅ ከመሰል እኩይ ተግባራት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚሳተፉ ወገኖች ራሳቸውን ማቀብ ይኖርባቸዋል፡፡
ለአገራችን ከፍተኛ ፋይዳ ያለው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ዝግጅት እየተጠናቀቀ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ስልጣን በተሰጠው አካል ያልተፈቀደና የደህንነት ስጋት የሚፈጥር የሕገወጥ ሰልፍ ቅስቀሳ ማድረግ ተገቢነት የሌለው ሁከትና ብጥብጥ መፍጠርን ያነገበ የሴረኞች ድብቅ አጀንዳ ማስፈፀሚያ በመሆኑ ህዝባችን ይህን እኩይ ተግባር በፅኑ ሊያወግዙ እና ሊኮንኑ ይገባል።
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ማንኛወም ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚካሄዱና የሀገርና የህዝብ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም እንቅሳቃሴ ይቃወማል።
መንግስት ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ህገመንግስታዊ ተግባርና ኃለፊነቱን ለመወጣት በሚያደርገው እንቅሳቃሴ ሁሉ ሕዝባችን አሰፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደረደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የካቲት 03 ቀን 2015 ዓ.ም
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ሠመራ