በአፋር ክልል በግጭቱ ትምህርት አቋርጠው የነበሩ 368 ትምህርት ቤቶች ስራ ጀምረዋል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል በግጭት ምክንያት ትምህርት አቋርጠው የነበሩ 368 ትምህርት ቤቶች ዳግም ትምህርት እየሰጡ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ዳግም ትምህርት መስጠት ከጀመሩት ትምህር ቤቶች ውስጥ 358ቱ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ፥ አስር የሚሆኑት ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በአፋር ክልል ዞን 2 ውስጥ የሚገኙ 6 ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች እና 202 አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች አስፈላጊው እገዛ ተደርጎላቸው ትምህርት እየሰጡ መሆኑን በሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አመለውርቅ ሕዝቅኤል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በዞን አራት ውስጥ የሚገኙ 4 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 156 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ዳግም ተቀብለው ትምህርት እየሰጡ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርት አቋርጠው ስራ ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶችን ዳግም ለማስጀመርም የዳሳሳ ጥናት በማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ