Fana: At a Speed of Life!

ከፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

መንግሥት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተከሰተው ወቅታዊ ሁኔታ በገለልተኝነት መርህ በውይይት፣ በሰላማዊ መንገድ እና የቤተክርስቲያኒቱን ውስጣዊ አሠራር በጠበቀ ምልኩ መፍትሄ እንዲያገኝ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህ ጥረት ተሳክቶ የሃይማኖት አባቶች ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተስማምተዋል፡፡

የፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ጉዳዩን ለራሳቸው የፖለቲካ ፍላጎት ማሳኪያ ለማድረግ ሕገወጥ ሰልፎችን ተገን በማድረግ ሁከትና ግርግር ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የውስጥና የውጭ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ከእኩያ አላማቸው እንዲታቀቡና ኅብረተሰቡም ከሚመለከተው አካል እውቅና ባልተሰጠው ሰልፍ እንዳይሳተፍ ቀደም ሲል መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

በመሆኑም የፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች ሰሞኑን ካጋጠመው ችግር ጋር በተያያዘ በሁለቱም ወገኖች ለየካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም የተጠራው ሰልፍ እንዲቀር መወሰናቸው ከሀገር ህልውናና ከዜጎች ደኅንነት መጠበቅ አንጻር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ አክብሮቱን ያቀርባል፡፡

የእምነቱ አባቶች ጉዳዩ በሰላምና በውይይት እንዲፈታ ያሳዩት ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት የሚደነቅ መሆኑን የጋራ ግብረ-ኃይሉ እየገለጸ፤ በሂደቱ ለተሳተፉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ባለሀብቶች እና ታዋቂ ሰዎች ምስጋናውን ያቀርባል፡፡ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የችግሮችን ምንጭ፣ መንስኤና ተከታታይ ውጤቶች በጥልቀት ሲገመግም፣ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ሲሰበስብ መቆየቱን ያስታወቀው የጋራ ግብረ-ኃይሉ፤ ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የተነሳውን አጀንዳ ሽፋን አድርገው አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች በሰልፍ ሰበብ ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች መኖራቸው እንደተደረሰበት ያስታውቃል፡፡

ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የተነሳውን ጥያቄ በመጥለፍ፤ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ ለመጣል ቅንጅት የፈጠሩት የውጭና የውስጥ ኃይሎች ብጥብጥና ሁከትን አይነተኛ የስርዓት ለውጥ የሚያመጣ ስልት በማድረግ በህቡዕ ሲያሴሩ፣ ሲቀሰቅሱ፣ ፋይናንስና ሎጀስቲክስ ሲያሰባስቡ እንደነበር የፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ባደረገው ክትትል ደርሶበታል፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያን ህልውናና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ፣ለማረጋገጥና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያስችሉ እርምጃዎች መውሰድ መጀመሩን የጋራ ግብረ-ኃይሉ እየገለጸ፤ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሚኖሩ ወቅታዊ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ይፋ የሚያደርግ መሆኑንም ያሳውቃል፡፡

የጋለ ምጣድ እየፈለጉ የግጭት እንጎቻ በመጋገር ሀገርን ለጠላት እንዲሁም ዜጎቿን ለአደጋ በማጋለጥ ራስ ወዳድ የፓለቲካ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሌት ተቀን የሚሠሩና የሚተጉ ቅጥረኛ ፓለቲከኞች እንዲሁም ጉዳዩን በማባባስ የተላላኪነት ሚናቸውን ለመወጣት ሲሞክሩ የነበሩ የተለያዩ የሚዲያ አውታሮችም እንደትናንቱ ዛሬም ከስረዋል፣ በቀጣይም ይከስራሉ።

እነዚህ ኃይሎች የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ እንደ እድል በመጠቀም ጊዜያቸውን፣ ሀብታቸውንና ምኞታቸውን ሁሉ ግጭት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በመረጃ የተረጋገጠ ጉዳይ ሲሆን፤ በመንግሥታችን አርቆ አሳቢነት፣ በሰላም ወዳድ ሕዝባችን እና በታላላቅ የሃይማኖት አባቶቻችን የሀገርን ሰላም ማዕከል ያደረጉ በሳል ውሳኔዎች የግጭት ፍላጎቶች እንዲከሽፉ በመደረጉ ዝግጅታቸው ከንቱ እንዳይቀር የሸረቡትን ሴራ ለማሳካት መውተርተራቸው የሁል ጊዜ ተግባራቸውና ምኞታቸው መሆኑን እናውቃለን፡፡

በመሆኑም የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ ይህን እኩይ ሴራቸውን በማክሸፍ የኢትጵያን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ ሥራ መጀመሩን ይገልጻል፡፡ በዚህ መሰረትም በአዲስ አበባና በአጎራባች አካባቢዎች ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ለሥራ ከተፈቀደላቸው
የፀጥታና ደኅንነት አካላት ውጪ ማንኛውም ሰው የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑን የተቋቋመው የጋራ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት ያስታውቃል፡፡ እንዲሁም ኅብረተሰቡ እራሱን፣ ቤተሰቡንና ልጆቹን ከማንኛውም ሰልፍ ወይም ሁከትና ግርግር ከሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች እንዲጠበቁ ማድረገ እንደሚገባው የጋራ ግብረ-ኃይሉ በአጽንዖት ያሳስባል፡፡

የፀጥታና የደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ፤ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ፀረ-ሰላም ኃይሎች የሀገራችንን ሰላምና ደኅንነት ለማደፍረስ የሚያደርጉትን ጥረቶችን ለማምከን የተቀናጀ ስምሪት ወስዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን እየገለጸ፤ ከእምነት ተቋማት ደኅንነት ጋር በተያያዘ ተገቢው ጥበቃ የሚደረግ በመሆኑ የሃይማኖት አባቶችና ምዕመናን ምንም አይነት ስጋት እንዳያድርባቸው ያስገነዝባል፡፡

በመጨረሻም ዜጎች እንደተለመደው ሁሉ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ አካባቢያቸውን በንቃት በመጠበቅ አጠራጣሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት በ987፣ 991 ፣ 816 እና 910 ነፃ የስልክ መስመሮች እንዲሁም በስልክ ቁጥር 011-1-11-01-11፣ 251115-52-63-03፣ 251115-52-40-77፣ 251115-54-36-78 እና 251115-54-36-81 ጥቆማዎችን በፍጥነት በመስጠት ወይም በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች መረጃውን በአካል በማድረስ ቀና ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የጋራ ግብረ ኃይሉ ኮማንድ ፖስት ጥሪውን ያቀርባል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና
የአዲስ አበባ ፖሊስ
የካቲት 04 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.